የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን የክለቡ የበላይ አመራሮች እና ደጋፊዎቹ በተገኙበት በአሁኑ ሰዓት በሸራተን አዲስ ሆቴል እያከናወነ ይገኛል። በዚህም መድረክ ላይ በኢትዮጵያ ክለቦች ታሪክ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ መጠን እንዳገኘ ተነግሯል።
በዚህም መሠረት ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ እና ዳሸን ባንክ እያንዳንዳቸው ሁለት መቶ ሚልዮን ብር፣ ቢጂአይ ኢትዮጵያ ሃምሳ ሚልዮን ብር እና ፔፕሲ ሰማንያ ሁለት ሚልዮን ብር በድምሩ 532 ሚልዮን ብር በዓመት ለቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር እንደሚከፍሉ ተነግሯል።

በተጨማሪም የክቡር ይድነቃቸው ተሰማ አካዳሚን ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን እየተሰራ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን ከፖርቹጋል ኃያል ክለብ ቤነፊካ ጋር በጋራ ለመስራት ስመምነቱ ወደ መጠናቀቁ እንደተቃረበ ሲሰማ ለዚህም አካዳሚ የሚውል ገንዘብን ከማስተር ካርድ 1.5 ሚልዮን ዶላር ማስገኘት መቻሉን ተጠቁሟል። የክለቡ የበላይ ጠባቂ የሼህ መሐመድን አሊ አላሙዲን ለክለቡ ከቢሾፍቱ ወደ ሞጆ በሚወስደው መንገድ ላይ 32 ሺህ ካ.ሜ መሬት የሰጡ መሆኑም ታውቋል።
ክለቡ ሊያስገነባው ያሰበውን ዘመናዊ ስታዲየምን ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በራሱ ወጪ እንደሚገነባ ተነግሯል።

