ፕሪምየር ሊግ ትኩረት 21 | ተናቋሪዎቹ የክለብ ልሳኖች

ፕሪምየር ሊግ ትኩረት 21 | ተናቋሪዎቹ የክለብ ልሳኖች

“ኮስታራነት” በሚያጠቃው እግር ኳሳችን ፊትን ከሚያጨፈግጉ አጀንዳዎች ባሻገር ሳቅ ጨዋታን የሚያስተናግድ ትከሻን መፍጠር ይኖርብናል።

የኢትዮጵያ እግር እግር ኳስ በብዙ መመዘኛዎች ከዓለም እግር ኳስ ጋር ሆድና ጀርባ ሆኖ በቀጠለበት በዚህ ዘመን የሀገር ውስጥ እግር ኳስ በማህበረሰቡ ዘንድ የሚያገኘውን ትኩረት ለማሳደግ የሚረዱ የትኛዎቹንም ዘዴዎች እግር ኳሳችን አስሶ መተግበር ለነገ የማይባል የዛሬ የቤት ስራችን ነው።

ከእነዚህ ጥረቶች መካከል የወቅቱ የትኩረቶች ሁሉ የስበት ማዕከል በሆነው ዲጂታሉ አውድ ለወትሮው ሩቅ ይባል በነበረበው እግር ኳሷችን በአንዳንድ ክለቦች በኩል ዘመኑን የዋጁ ይዘቶች መንሸራሸር ጀምረዋል ይህም ለዓለምአቀፋዊ ተሞክሮዎች ብርቅ ለሆነበት ሊጋችን ሰሞነኛው የመነጋገርያ ጉዳይ ለመሆን በቅቷል።

አዳዲስ ሀሳቦችን መፍጠር ይቅርና የሌሎችን በጎ አካሄድ በወጉ ለመኮረጅ እንኳን ይቸገር የነበረው ሊጋችን አሁን ግን ምስጋና ለዲጂታሉ ዘመን ትውልድ ይግባና ከደጋፊዎች የተለመደ እግር ኳሳዊ ቅኝት ያላቸው “መነቋቆሮች” ወደ ይፋዊ የክለብ ልሳኖች ነቆራ ሽግግሩን በይፋ ጀምረናል።

የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ብሎም ይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገፆች ብርቅ በሆነበት ሊጋችን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን በክለቦቹ ስም የተከፈቱ በተከታታይ ልጥፎችን የሚጋሩባቸው ገፆች ተበራክተዋል ፤ ስለ ትክክለኝነታቸው ማረጋገጫ ማቅረብ ባይቻልም “ይፋዊ” የክለብ ልሳን ነን በሚሉት በእነዚህ ገፆች ከተለመዱት “ኮስታራ” ይዘቶች ባሻገር ገቢር ነበብ (Trending) የሆኑ ይዘቶች እንዲሁ ሲጋሩ በስፋት እያስተዋልን እንገኛለን ፤ በዚህም ሂደት ውስጥ በተፎካካሪ ቡድኖች ላይ ቀልድ የሚያጭሩ ሀሳቦች መንሸራሸር የብዙሃኑን ቀልብ የገዛ ጉዳይ ነበር።

ይህ አካሄድ አይደለም ክለቦች በዓለም አቀፍ ደረጃ በብዙ ቢልየን ዶላር የሚያንቀሳቅሱ ግዙፉ ኩባንያዎች ሳይቀር በተለመደው መንገድ ምርትና አገልግሎታቸውን ከማስተዋወቅ ይልቅ ፈገግታን በሚያጭር በግርድፉ ሲታዩ “አሁን ይሄ ከእነሱ ይጠበቃል?” በሚባሉ ይዘቶችና ተፎካካሪዎቻቸው ላይ ስላቅን በመፍጠር በሰዎች ዘንድ በቀላሉ በማይዘነጉ እና አዝናኝ በሆነ መንገዶች ገፅታቸውን እየገነቡ ይገኛል።

ይህ አዲስ ልምምድ የሀሳብ ነፃነቶች ይከርባቸዋል በሚባሉት በአደጉት ሀገራት አሁን ላይ ከመለመድ አልፎ እንደ አንድ የይዘት ዘርፍ ተቆጥሮ እየተሰራበት የሚገኝ ቢሆንም ከውዳሴ ውጪ ትችት ጠል በሆነው እግር ኳሳችን አዲስ ልምምድ እንደመሆኑ በሙከራው ብዙሃኑ የእግር ኳስ ቤተሰብ መደናገጡ አልቀረም ፤ ይህ አካሄድ ገና ጅምር ላይ እንደመሆኑ መደናገጡ ብሎም የተወሰኑትን ማስቆጣቱ የሚጠበቅ ቢሆንም በሂደት ይህ አዲስ ጅምር እየተለመደ ሲመጣ ልጥፎቹ ከሳቅና ጨዋታ መፍጠሪያነት የዘለለ ግብ እንደሌላቸው ለመረዳት የሚያስችል ትከሻ በብዙሃኑ ዘንድ ይፈጠራል ተብሎ ይገመታል።

እንደ ሀገር ያለን የዲጂታል ንቃተ ህሊና እርግጥ መሻሻል ላይ ቢገኝም አሁንም ድረስ በሚፈለገው ደረጃ ላይ አይገኝም በመሆኑም መሰል ይዘቶችን የሚያጋሩ ክለቦች ይህን ድርጊት ፍፁም ሃላፊነት በተሞላበት መንገድ መወጣት የግድ የሚላቸው ሲሆን በዚህ ረገድ የምትሰራ ጥቂት ስህተት የምታስከፍለው ዋጋ የላቀ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል ፤ ገፆችን የምንከታተል ብዙሃን ደግሞ ልጥፉን በተለያየ መነፅር ከመመልከት ተቆጥበን የሚጋሩትን ሀሳቦች በእግር ኳሳዊ ማነፀሪያ አንፃር መመልከት ይገባል መልዕክታችን ነው።

ይህን አዲስና የመጪው ዘመን መንገድ እንደሆነ የሚታመንበትን አካሄድ የተወሰኑ የሀገራችን ክለቦች ከወዲሁ የጀመሩት ሲሆን አመዛኙ የሊጉ ክለቦች ግን አሁንም የማህበራዊ ትስስር ገፅ አልከፈቱም የከፈቱትም ገፃቸው ፆሙን ማደሩን ተያይዞታል በመሆኑም ክለቦቻችን አሁን ሳይረፍድ በዚህ የለውጥ ባቡር ውስጥ መሳፈር የግድ ይላቸዋል።

መሰል መነሻቸውን ሆነ መድረሻቸው ተዝናኖትን በመፍጠር የምትገኘውን ዲጂታል ትኩረት (Engagement) ለመጠቀም የሚደረጉ ሙከራዎች ስርዓት ባለው አውድ እስከተቃኙ ድረስ ትኩረት ለተነፈገው ኳሷችን ሌላ ማጣፈጫ ቅመም እንደሚሆኑ ይጠበቃል።