አዲስ የውድድር ዘመን ተመሳሳይ አዝማሚያዎች ፤ ከዚህ አዙሪት መች ይሆን የምንወጣው?

የኢትዮጵያን እግር ኳስ የሚከታተል የትኛውም ሰው ሊጋችን በተለይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በገጠመው የተመልካቾች ድርቅ ያላዘነ አልነበረም ፤ ዘንድሮ ግን በተደረገው የሊጉ የፎርማት ማሻሻያ ገና በ4 ሳምንታት በተመለከትነው ተስፋ ሰጪ የተመልካቾች ቁጥር አስደሳች ቢሆንም ገና በወጉ ተደስተን ሳንጨርስ ብዙሃኑን ስጋት ውስጥ የሚከት የእግር ኳሳችን የቀድሞ አዙሪት ምልክቶችን ከወዲሁ መመልከት ጀምረናል።
የውድድር ዘመኑ ከተጀመረ ገና 4ኛ ሳምንት ላይ ቢገኝም አንዳንድ ሜዳ ላይ የምናያቸው ክስተቶች ሊጉ ሊጠናቀቅ 4 የጨዋታ ሳምንታት የቀሩት የሚያስመስሉ ናቸው ፤ በእንቅስቃሴ ወቅት የሚፈጠሩ የተለመዱ በተጫዋቾች መካከል የሚፈጠሩ አካላዊ ንኪኪዎችን መነሻ በማድረግ ሜዳ ላይ ጦር የሚሰብቁ አንዳንድ “ሀሰተኛ የመለያ ዘብ” ነን ባዮች ከወዲሁ የሚያደርጉትን ሃላፊነት የጎደለው ተግባርን ለተመለከተ በ4 ሳምንታት ተመልክተን ያልጠገብነው የተሟሟቀ የስታዲየሞች ስሜትን በአሉታዊ ስሜቶች እንዳይበርዙብን የሚያሰጋ ነው።
የሜዳ ላይ ጉሽሚያና ፍትጊያዎች ያሉ እና የሚኖሩ ቢሆንም በረባ ባረባው ሜዳ ላይ ለፀብ መጋበዝ ብሎም ክለቡን ሊደግፍ የመጣ ተመልካችን በተሳሳተ መንገድ ላልተገባ ድርጊት እንዲነሳሳ ማድረግ ከስህተትነት አልፎም እንደ ነውር ሊወገዝ የሚገባ ተግባር ነው።
እርግጥ እግር ኳስ የላቀ ስሜት ስፓርት ቢሆንም መሰል የጀብደኝነት ተግባራት ግን ለመለያ ከመቆርቆር የሚመነጩ ሳይሆን በአመዛኙ የግለሰባዊ ግብዝነት መገለጫ ናቸው ፤ ተጫዋቾች ለለበሱት መለያ ሆነ ለክለባቸው ያላቸውን ክብርና ፍቅር የሚያሳዩት በሜዳ ላይ ያላቸውን ሁሉ በመስጠት እንጂ በይዋጣልን ስሜት ደረትን ነፍቶ ለያዥ ለገላጋይ በማስቸግር አይደለም።
በአዲሱ የሊግ ፎርማት ሊጉ በ7 ከተሞች እንዲደረግ የመወሰኑ ጉዳይ ወደ ሜዳ የተሻለ የደጋፊ ቁጥር ይዞልን እየመጣ ቢሆንም የመጣውን ደጋፊ በስታዲየሞች ማቆየት ግን ትልቅ ስራ ይጠይቃል ፤ ደጋፊ ወደ ሜዳ የሚመጣው በዋነኛነት ጥሩ የሜዳ ላይ ትርዒት ለማየት እንደመሆኑ ሜዳ ላይ ስለሚታየው ትርዒት ማማር አሰልጣኝ እና ተጫዋቾች የላቀ ሃላፊነት አለባቸው ነገርግን ጥቂቶች ሜዳ ላይ የተሻለ ብቃት ለማሳየት ከመታተር ይልቅ ደካማ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴያቸውን በፀብ አጫሪነትና ለክለባቸው ዘብ በመመሰል ደጋፊን ለማታለል ሲሞክሩ ይታያል።
ሊጋችን ድህረ ኮቪድ በተመረጡ ሜዳዎች እንዲካሄድ መደረጉ ሊጉን ከተመልካቾች ቀልብ ቢያርቅም በስታዲየሞች ፀጥታ ረገድ የነበረብንን ክፍተት ግን በተወሰነ መልኩ ምላሽ ያስገኘ ነበር ፤ አሁን ውድድሩ ወደ ተለያዩ ከተሞች እንዲወጣ መደረጉ በተለይ ሜዳ ውስጥ ያሉ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ስሜታቸውን መግራት ካልቻሉ በእነርሱ ሃላፊነት የጎደለው ምግባር በስታዲየሞች ውስጥ ለሚፈጠሩ ስርዓት አልበኝነቶች መነሻ እንዳይሆነ የሚያሰጋ በመሆኑም አወዳዳሪው አካል መሰል አዝማሚያዎች ላይ ጠንከር ያሉ ቅጣቶች በማሳለፍ ከወዲሁ ይህን ዝንባሌ ከምንጩ ማድረቅ ይጠበቅበታል።

