ፕሪምየር ሊግ ትኩረት | መጠበቅ የፈጠረው ጫና?

ፕሪምየር ሊግ ትኩረት | መጠበቅ የፈጠረው ጫና?

ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና አዲሱን የውድድር ዘመን ሲጀምሩ ከፍ ባለ ተጠባቂነት ውስጥ ሆነው ነበር አጀማመራቸው ግን በተጠበቀው ልክ አልሆነም ለምን ?

የሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥን ከ4ኛ የጨዋታ ሳምንት በኋላ ላስተዋለ ሁለቱ የመዲናይቱ ክለቦች ታላላቅ ክለቦች በእኩል 3 ነጥብ 12ኛና 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል ፤ እርግጥ ሊጉ ገና ቀሪ የ30 ሳምንታት ጉዞ ቢጠብቀውም የሁለቱ ቡድኖች አጀማመር ግን ይበልጥ ትኩረት የሚስብ ነው።

የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ቡድናቸው በኢትዮ ኤሌክትሪክ ከተሸነፈበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ በድህረ ጨዋታ አስተያየታቸው ካነሷቸው ሀሳቦች መካከል አንዱ ተጫዋቾቻቸው ላይ በተለይም ከፍተኛ ተጠባቂነት ባለበት ክለብ ውስጥ ከመጫወት አንፃር የሚስተዋል “ጭንቀትን” በምክንያትነት ያቀረቡ ሲሆን ይህን ለመሸገር ከተጫዋቾቻቸው የላቀ አዕምሮአዊ ጥንካሬም እንደሚጠበቀን አንስተዋል ፤ በተመሳሳይ የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ሚሉቲን ሚቾም እንዲሁ ከሸገር ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ በሰጡት አስተያየት በዚህ ልክ በርካታ ወጣቶች የሞሉበት ስብስብ ጋር ሲሰሩ የመጀመሪያቸው መሆኑን አንስተው ከመመራት ተነስተው ነጥብ የተጋሩበትን ሁኔታም ሲያስረዱ ተጫዋቾቻቸው በእጃቸው የገባውን መሪነት ለማስጠበቅ የተሻለ አዕምሮአዊ ጥንካሬም እንደሚያስፈልጋቸውም እንዲሁ ገልፀዋል።

ከሁለቱ አስተያየቶች መረዳት የሚቻለው አሁን ላይ ሁለቱም ቡድኖች በአዕምሮአዊ መመዘኛዎች አሰልጣኞቻቸው በሚፈልጉት ደረጃ ላይ እንደማይገኙ ነው።አዕምሮአዊ ጥንካሬ?

መደበኛ ቡድኖች እና በአሸናፊ ቡድኖች መካከል ያለው መሰረታዊ ልዩነት አዕምሮአዊ ጥንካሬ ዋንኛው ነው ፤ ስፔናዊው አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ እንደሚለው የተጫዋቾት ኳሊቲ ሁሌም ይኖራል ነገርግን ዋነኛው ልዩነት የሚፈጥረው ጉዳይ የተጫዋቾች አዕምሮአዊ ዝግጁነት ነው ይላል። አዕምሮአዊ ጥንካሬ(ዝግጁነት) መገለጫው ብዙ ነው።በጨዋታ ወቅት ማድረግ የሚፈልገውን በግልፅ የሚያውቅ ፣ ስሜቱን የሚቆጣጠር ፣ ከስህተቶች በኃላ በፍጥነት ወደ ማንነቱ የሚመለስና በጫና ውስጥ ቢሆን እንኳን የተሻለ ውሳኔዎችን መወሰን መቻል መገለጫዎቹ ናቸው።

ይህ ጉዳይ በተለይ ተጫዋቾች በዚህኛው ከፍ ባለው ደረጃ በጫና ውስጥ መጫወትን እየለመዱ ሲመጡ በሂደት እንደሚሻሻል ቢጠበቅም እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ባሉ ውጤትን አብዝተው በሚጠብቁ ቡድኖች ውስጥ ይህን ሂደት ፈጣን እንዲሆን ይጠበቃል ፤ በርካታ በዚህ ደረጃ የመጫወት ልምድ የሌላቸው ተጫዋቾችን የያዙት እነዚህ ሁለት ቡድኖች ካለባቸው ከፍ ያለ ተጠባቂነት ስሜት ጋር ተዳምሮ ይህን ተግዳሮት እንዴት ይሻገሩታል የሚለው ጉዳይ በቀጣይ ይጠበቃል።

በሁለቱም ቡድኖች አመራሮች ሆነ ደጋፊዎች ዘንድ ዘንድሮ የሊጉን ዋንጫ የማንሳት ከፍ ያለ መሻት ባለበት በዚህ ወቅት የእያንዳንዱ ጨዋታ ዋጋ ከወትሮው የላቀ ይሆናል።የሁለቱን ቡድኖች ደካማ አጀማመር ይበልጥ ትኩረት እንዲስብ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ሁለቱም ቡድኖች አራቱንም ጨዋታቸውን በሜዳቸው እና ደጋፊያቸው ፊት የማድረጋቸው ጉዳይ ነው ፤ ለዋንጫ መጫወት የሚያልም ቡድን በሜዳው ሆነ ከሜዳው ውጭ ማሸነፍ ግዴታው እንደሆነ ቢታመንም በአዲስ መልኩ በአዲስ አሰልጣኝ እየተገነቡ ላሉት ሁለቱ ቡድኖች በሜዳቸው እና በደጋፊያቸው ፊት ተከታታይ አራት ጨዋታዎችን ከማድረግ በላይ ለሊግ አጀማመር የተሻለ ዕድል (Advantage) ፈልጎ ማግኘት ከባድ ነው።እንደ አዲስ እየተገነቡ የሚገኙት ሁለቱ ቡድኖች በእነዚህ ጨዋታዎች በደጋፊዎቻቸው ታግዘው የቡድኑን የራስ መተማመን የሚያሳድጉ የተሻሉ ነጥቦች ያገኛሉ ተብሎ ሲጠበቅ የሆነው ግን በተቃራኒ ነው።

በመሆኑም የሊግ ውድድር በማራቶን እንደመወከሉ 34ኛው የጨዋታ ሳምንት ላይ ሁለቱም ክለቦች ካለሙበት የሊጉ አናት ለመገኘት ክፍተቶቻቸውን ደፍነው በተለይ በሜዳቸው በቀጣይ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች የቡድኖቻቸውን የራስ መተማመን ማሳደግ የሚያስችሉ ወሳኝ ድሎችን ማስመዝገብ የውድድር ዘመናቸውን በፍጥነት ወደ መስመር ለመመለስ ያስችላቸዋል ተብሎ ይታመናል።