የ7ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል

የ7ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል

በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 7ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከሀዲያ ሆሳዕና እንዲሁም ፋሲል ከነማ ከኢትዮጵያ መድን በአንድ አቻ ውጤት ተለያይተዋል።

በዐቢዩ አረጋሽ

9፡30 ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ሀዲያ ሆሳዕና 1ለ1 በሆነ ውጤት አቻ ተለያይተዋል።

በጨዋታው 11ኛው ደቂቃ ላይ አሸናፊ ኤልያስ ከቀኝ መስመር ወደ ሳጥን ያሻገረውን ኳስ ቢኒያም ጌታቸው በግንባሩ በመግጨት ወደ ግብነት ቀይሮ ሀዲያ ሆሳዕናን መሪ ማድረግ ችሏል።

በቀሪው የመጀመሪያ አጋማሽ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በኳስ ቁጥጥር የተሻለ አፈጻጸም ቢያሳይም፣ የተሻሉ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር በኩል ሀድያ ሆሳዕና የተሻለ ነበረ። በዚህም የመጀመሪያው አጋማሽ በሀድያ ሆሳዕና 1ለ0 መሪነት ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ኢትዮ ኤሌክትሪክ የአቻነት ግብ ፍለጋ ጥረቱን ቀጥሏል። በመጨረሻም 90ኛው ደቂቃ ላይ ቶሎሳ ንጉሤ በፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ኳስን በእጁ በመንካቱ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት አስቻለው ታመነ ወደ ግብነት በመቀየር ኢትዮ ኤሌክትሪክን አቻ አድርጓል። ጨዋታውም 1ለ1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

 

በሌላው የዕለቱ ጨዋታ በ10፡00 ሰዓት በባህር ዳር አለም አቀፍ ስታዲየም ፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ መድን 1ለ1 በሆነ ውጤት አቻ ተለያይተዋል።

በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ፋሲል ከነማ በኳስ ቁጥጥርና የግብ ዕድሎችን በመፍጠር የተሻለ አፈጻጸም አሳይቷል። በተቃራኒው ኢትዮጵያ መድን ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርግ የወጣ ሲሆን፣ የመጀመሪያው አጋማሽ ያለ ግብ 0ለ0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ በ59ኛው ደቂቃ ኢትዮጵያ መድን በመልሶ ማጥቃት ያገኘውን ዕድል ሳሙኤል ሳሊሶ ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን መሪ አድርጓል። በዚህም መድን በጨዋታው የተፈጠረበትን ጫና በመቋቋም ወደ መሪነት መምጣት ችሏል።

ሆኖም በ81ኛው ደቂቃ አብዱመሐመድ በፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ጥፋት ሠርቷል በሚል ለፋሲል ከነማ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ወደ ግብነት በመቀየር ፋሲል ከነማን አቻ አድርጓል።

በዋና ዳኛው የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት በመቃወም ደስተኛ ያልነበሩት የኢትዮጵያ መድን አሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብተዋል። ጨዋታውም 1ለ1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

በዚህም የሊጉ 7ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች በሁለቱም ጨዋታዎች አንድ አንድ ነጥብ በመጋራት ተጠናቀዋል።