ደደቢት የአፍሪካ ጉዞውን በድል ጀመረ

የ2005 የፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮን ደደቢት የዛንዚባር ሻምፒዮኑ ኬኤምኤኤምን አስተናግዶ ከፍፁም የጨዋታ የበላይነት ጋር 3-0 አሸንፎ ወጥቷል፡፡

በሰማያዊ ቀላማት አሸብርቆ የዋለው አዲስ አበባ ስታዲየም አብዛኛው የስታዲየም ክፍል በተመልካች የተሞላ ሲሆን የደደቢት ደጋፊዎች በካታንጋ በህብረ ዜማ ታጅበው ቡድናቸውን አበረታተዋል፡፡

ደደቢት የጨዋታ ማስጀመርያ ፊሽካ ከተሰማበት ደቂቃ ጀምሮ ሙሉውን 90 ደቂቃ በኳስ ቁጥጥር እና የግብ እድሎች በመፍጠር በኩል ብልጫ አሳይቷል፡፡

በመጀመርያው አጋማሽ 10 ደቂቃዎች 3 ግልፅ የማግባት አጋጣሚዎች ቢያገኙም ዳዊት ፍቃዱ እና ሽመክት ጉግሳ ወደ ግብ መቀየር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ደደቢት የመጀመርያ ግቡን ያስቆጠረው በእለቱ የኬኤምኬኤም የተከላካይ ክፍልን ሲያስጨንቅ በዋለው ዳዊት ፍቃዱ አማካኝነት በ16ኛው ደቂቃ ነው፡፡ ከግቡ መቆጠር በኋላ ተደጋጋሚ የግብ ማግባት እድሎችን የፈጠረው ደደቢት ተጨማሪ ግቦች ማስቆጠር ሳይችል የመጀመርው አጋማሽ ተጠናቋል፡፡

ከእረፍት መልስ ከመጀመርያው አጋማሽ ተሽለው የቀረቡት ደደቢቶች ጥቃታቸውን አጠናክረው በ52 ኛው ደቂቃ በሽመክት ጉግሳ እንዲሁም በ84ኛው ደቂቃ ተቀይሮ በገባው ሚካኤል ጆርጅ ግብ አስቆጥረው ጨዋታውን 3-0 አጠናቀዋል፡፡

ደደቢት በሁለተኛው አጋማሽ ሁለት ግብ ከማስቆጠሩ በተጨማሪ በሳምሶን ጥላሁን ፣ ሽመክት ጉግሳ ፣ ሚካኤል ጆርጅ ፣ ዳዊት ፍቃዱ እና መስፍን ኪዳኔ አማካኝነት ከግማሽ ደርዘን የሚልቁ ሙከራዎችን ያደረገ ሲሆን መስፍን ኪዳኔ በሁለት አጋጣሚዎች ግብ አስቆጥሮ ከጨዋታ ውጪ ተብሎ ሳይቆጠርለት ቀርቷል፡፡

ደደቢት የመልስ ጨዋታውን በመጪው እሁድ ያደርጋል፡፡

{jcomments on}