የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌድሬሽን (ካፍ) የመጪው የአፍሪካ ዋንጫ የውድድር ፎርማት ይፋ አድርጓል፡፡ የምድብ ድልድሉም ኤፕሪል 8 ቀን 2015 ከአስተናጋጇ ሃገር ጋር አብሮ ያሳውቃል፡፡
የመጀመርያው የማጣርያ ጨዋታ ጁን 2015 የሚደረግ ሲሆን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ አስተናጋጅ ሃገር በማጣርያው ላይ ይሳተፋል፡፡ ነገር ግን አስተናጋጁ ሃገር የሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ነጥብ አይያዝም፡፡
በማጣርያው 52 ሃገራት የሚሳተፉ ሲሆን እያንዳንዳቸው 4 ብሄራዊ ቡድኖች የያዙ 13 ምድቦች ይኖራሉ፡፡ ከምድቡ አንደኛ የሚወጡ 13 ቡድኖች በቀጥታ ለአፍሪካ ዋንጫው ሲያልፉ ከምድባቸው በጥሩ ሁለተኝነት የሚያጠናቅቁ ሁለት ቡድኖች እና አስተናጋጇ ሃገር ወደ አፍሪካ ዋንጫ ያልፋሉ፡፡ ካፍ እንዳስታወቀው በተለያየ ምክንያት ከማጣርያው የሚወጡ ቡድኖች ከሚኖርባቸው ምድቦች ጥሩ 2ኛ ሃላፊ አይኖርም፡፡
በተያያዘ ዜና ካፍ የ2018 የሩስያ የአለም ዋንጫ የማጣርያ ፎርማትንም ይፋ አድረጓል፡፡ ኦክቶበር 2015 በሚጀምረው የማጣርያ ጨዋታ ከቀድሞው በተለየ ሁኔታ 3 የቅድመ ማጣርያ ጨዋታዎች ይኖሩታል፡፡ ሶስቱን ቅድመ ማጣርያዎች በአሸናፊነት የሚወጡ 20 ቡድኖች በ5 ምድቦች ተከፍለው የምድብ ማጣርያ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ፡፡ ከየምድቡ አንደኛ የሚወጡ አምስት ብሄራዊ ቡድኖችም አፍሪካን ወክለው በ2018 የሩስያ አለም ዋንጫ ላይ ይሳተፋሉ፡፡