የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አንደኛው ዙር ተስተካካይ ጨዋታዎች በአዲስ አበባ እና ክልል ከተሞች ተካሂዶ ደደቢት እና ኤሌክትሪክ ድል ቀንቷቸዋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ አንደኛውን ዙር በመሪነት የማጠናቀቅ እድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡
ወደ ሀዋሳ ያቀናው ደደቢት ሀዋሳ ከነማን 2-0 አሸንፎ ተመልሷል፡፡ የደደቢትን የድል ግብ ከመረብ ያሳረፉት ተከላካዩ ብርሃኑ ቦጋለ እና አጥቂው ዳዊት ፍቃዱ ናቸው፡፡ ደደቢት ድሉን ተከትሎ ከመሪዎቹ ያለውን ርቀት በመጠኑ አጥብቦ አንደኛውን ዙር ሲያጠናቅቅ ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ሀዋሳ ከነማ ደግሞ 13ኛ ደረጃን ይዟል፡፡
ቦዲቲ ላይ ወላይታ ድቻን የገጠመው ቅዱስ ጊዮርጊስ ካለግብ አቻ ተለያይቷል፡፡ ጊዮርጊሶች ጨዋታውን ካሸነፉ በግብ ልዩነት ሊጉን የመምራት እድል የነበራቸው ቢሆንም ነጥብ ትለው ተመልሰዋል፡፡
አበበ ቢቂላ ላይ ኢትዮጵያ ቡና ከ ኤሌክትሪክ ባደረጉት ጨዋታ ኤሌክትሪክ በፒተር ንዱንካ ግብ 1-0 አሸንፎ ነጥቡን ከፍ አድርጓል፡፡
የሊጉን አንደኛ ዙር ሲዳማ ቡና በ27 ነጥቦች መርቶ ሲያጠናቅቅ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ25 ፤ ወላይታ ድቻ በ22 ነጥቦች ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል፡፡ የከፍተኛ ግብ አግቢነቱን ደግሞ የኢትዮጵያ ቡናው ቢንያም አሰፋ በ11 ግቦች ይመራል፡፡