ኮንፌድሬሽንስ ካፕ ፡ ‹‹ ወጣቶቹ ተጫዋቾች ላይ መሻሻልን እያየሁ ነው ›› አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ

አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ በመጪው ቅዳሜ ከሲሸልሱ ኮት ዲ ኦር ክለብ ጋር ከሚያደርጉት ጨዋታ በፊት ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርገዋል፡፡

ስለ ቡድኑ ግብ የማስቆጠር ችግር

የመጀመርያው ምክንያት የአጥቂዎቻችን ቁጥር ማነስ ነው፡፡ ያሉኝ አጥቂዎች እጅግ በጣም ጥቂት በመሆናቸው የግብ ማስቆጠር ችግር በአንድና በሁለት ሳምንት ውስጥ የሚስተካከል አይደለም፡፡ ነገሮችን በዘላቂነት የምናስተካክልበት ጊዜ ባለማግኘታችን ከታክቲክ ጋር የተያያዙ ፈጣን ለውጦችን ለማምጣት እየሰራን ነው፡፡

ስለ ወጣት ተጨዋቾች ዝግጁነት

የኢንተርናሽናሉን ውድድር ገና የምናየው ነው፡፡ በሃገር ውስጥ ጨዋታዎች ስንመለከት ግን ወጣቶቹ ተጫዋቾች ከጨዋታ ጨዋታ እየተሻሻሉ ነው፡፡ በአካል ብቃታው ፣ በራስ መተማመናቸውና የታክቲክ ግንዛቤያቸው ላይ በየጊዜው ለውጦች እየተመለከትኩባቸው ነው፡፡ እንዴት ጫና መቋቋም እንዳለበባቸውም እየተረዱ መጥተዋል፡፡

ጉዳት ላይ ስላሉት ተጫዋቾች

ጉዳት ላይ ከነበሩት ውስጥ እስካሁን ለጨዋታው ሙሉ ለሙሉ ዝግጁ የሆነ ተጫዋች የለም፡፡ ታደለ ቢያገግምም ለ6 ሳምንታት ከሜዳ በመራቁ የአካል ብቃቱ ለጨዋታ ዝግጁ አይደለም፡፡ አክሊሉ ፣ ብርሃኑ እና መስፍን መስፍንም በጉዳት ምክንያት ለጨዋታ ብቁ አይደሉም፡፡

ስለ ተጋጣሚያቸው

ስለ ተጋጣሚያችን መረጃ የለንም፡፡ የአፍሪካ ውድድሮች ልምድ ያለው ቡድን እንደሆነ እናውቃለን፡፡ የአየር ንብረቱም ተለዋዋጭ ነው፡፡ እስከ 31 ዲግሪ ሴልሽስ የሚደርስ ሙቀት ቢኖርም ድንገተኛ ዝናብ እንደሚጥል ስምተናል፡፡ ስለ ክለቡ የምናውቀው ይህን ነው፡፡

ስለ አዲሱ ግብ ጠባቂ ሱሌማና ቡባካሪ

ሱሌማና በቅዳሜው ጨዋታ ላይ መሰለፍ ይችላል፡፡ የኢንተርናሽናል የዝውውር ሰርቲፍኬት አግኝነተናል፡፡ታሪክ ጌትነት በመጎዳቱ ስንጠቀምበት የነበረው ሶፎንያስ ሰይፉ ገና ልምድ እያገኘ ነው፡፡ ሶፎንያስ ጥሩ ግብ ጠባቂ ቢሆንም ጫና ያለው ጨዋታ ላይ ማሰለፍ ለሱም ጥሩ አይሆንም፡፡ ሱሌማና ከፍተኛ ልምድ ያለው ግብጠባቂ በመሆኑ ይጠቅመናል ብለን እንስባለን፡፡

ስለ ምክትሉ ዳንኤል ፀሃዬ

ዳንኤል አብሮን ይጓዛል፡፡ የኢትዮጵያ ከ23 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ በመሆኑ ከክለቡ ፍቃድ እየወሰደ ሃገሩንም እያገለገለ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *