ኢትዮጵያዊው አጥቂ ፍቅሩ ተፈራ በደቡብ አፍሪካ አብሳ ፕሪምየርሺፕ ለአዲሱ ክለቡ ቤደቬስት ዊትስ ማክሰኞ ምሽት በተደረገ ጨዋታ ማርቲዝበርግ ዩናይትድ ላይ ግብ አስቆጠረ፡፡
ፍቅሩ በመጀመሪያው ጨዋታው ለዊትስ ግብ ማስቆጠሩ አስገራሚ ሆኗል፡፡ ማርቲዝበርግ ዩናይትዶች በጨዋታው መምራት ቢችልም ዊትስ 2 ግቦችን አስቆጥሮ 2ለ1 በሆነ ውጤት አሸንፎ ወጥቷል፡፡ ለዊትስ 2ኛውን ግብ ኢትዮጵያዊው ፍቅሩ ተፈራ የመጀመሪያው ግማሽ ሊጠናቀቅ በተቃረበበት ጊዜ በግምባር በመግጨት አስቆጥሯል፡፡ ፍቅሩ ለአዲሱ ክለቡ 12 ቁጥር መለያ ተስጥቶታል፡፡
በ6 ወር ውል ቤድቬስት ዊትስ የተቀላቀለው ፍቅሩ በመጀመሪያው ጨዋታ ግብ ማስቆጠሩ አሰልጣኝ ጋቭን ሃንትን አስደስቷል፡፡ ዊትስ በሊጉ ደረጃ ሰንጠረዥ በ34 ነጥብ 3ኛ ነው፡፡ ከመሪው ካይዘር ቼፍስ ጋር የ12 ነጥብ ልዩነት አለ፡፡ በተያያዘ ዜና ሌላኛው አትዮጵያዊ አጥቂ ጌታነህ ከበደ የተጠባባቂ ወንበር ላይ መቀመጡን ቀጥሎበታል፡፡ ጌታነህ ለዊትስ ተስልፎ ለመጫወት ተስኖታል፡፡