ኤም ሲ ኤል ኡልማ – የክለብ ዳሰሳ

በዘንድሮው የአፍሪካ የክለብ ውድድሮች ሰሜን አፍሪካዊቷ አልጄሪያ 5 ክለቦችን በማሳተፍ (3 በቻምፒዮንስ ሊግ፤ 2 በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ) ቀዳሚነቱን ይዛለች። ከነዚህ ክለቦችም በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ ማግኘት የቻለው እና የቅዱስ ጊዮርጊስ የቅድመ ማጣሪያ ተፋላሚ የሆነው ኤም ሲ ኤል ኡልማ ይገኝበታል። በዚህ ፅሁፍ ስለዚህ ክለብ ምስረታ፣ አደረጃጀት እና የአጨዋወት ፍልስፍና ሰፋ ያለ መረጃ እናቀርባለን።

MC-El-Eulma

ሙሉ ስም፡ ሞውሎውዲያ ክለብ ድ ኤል ኡልማ

ቅፅል ስም፡ ባቢያ

ምስረታ፡ 1936

ስታዲየም፡ ስታዴ መሳውድ ዘውጋር

ፕሬዘዳንት፡ ኢምባሬክ ቦውደን

አሠልጣኝ፡ አዘዲን አይት ጆውዲ

 

ኤል ኡልማ እ.ኤ.አ. በ1936 ዓ.ም. የተመሰረተ ሲሆን በሴቲፍ ግዛት የምትገኘው የኤል ኡልማ ከተማ አስተዳደር በባለቤትነት ይመራዋል። ከለቡ ከተመሰረተ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረና በዕድሜ የቅዱስ ጊዮርጊስ እኩያ ቢሆንም ወደ አልጄሪያ ፕሪምየር ሊግ መቀላቀል የቻለው ግን ከ7 ዓመታት በፊት የ2008ቱን የ2ተኛ ዲቪዝዮን ዋንጫ በማንሳት ነበር።

ክለቡ ባለፈው የአልጄሪያ ሊግ 1 (Algeria Championnat National 1) 4ተኛ ሆኖ ማጠናቀቅ የቻለ ሲሆን በሊጉ 2ተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ጄኤስ ካባሊዬ በካፍ በመቀጣቱ (ካሜሮናዊው አጥቂ አልበርት ኤቦሴ በካባሊዬ ደጋፊዎች በደረሰበት ጥቃት በመሞቱ ምክኒያት) እንዲሁም 3ተኛ ደረጃን የያዘውና አምና የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ባለድል የነበረው ኢኤስ ሴቲፍ በቀጥታ እንዲልፍ በመደረጉ ምክኒያት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ አፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ ለመሆን ችሏል።

ስታዲየም

Stadium

 

ስም – ስታዴ መሳውድ ዘውጋር

ባለቤት፡ የኤል ኡልማ ከተማ አስተዳደር

ተመልካች የመያዝ አቅም፡ 25000

ሜዳ፡ የተፈጥሮ ሳር

 

አሠልጣኝ1186370495

ሙሉ ስም – አዘዲን አይት ጆውዲ

የትውልድ ቀን፡ ጥር 24፣ 1967

የትውልድ ቦታ፡ ቴቤሳ፣ አልጄሪያ

ዕድሜ፡ 48

 

 

 

የ77 ኣመት ፈረንሳዊ ጁሌስ አኮርሲ በየካቲት እስከ ሰኔ 2014 ድረስ ቡድኑን ያሰለጠኑ ሲሆን በክለቡ ታሪክ ከፍተኛ ውጤት የሆነውን የ4ተኛ ደረጃ እና የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ እንዲያሳካ በማስቻል ከሃላፊነታቸው ወርደዋል። ጁሌስ አኮርሲን በመተካት ቡድኑን የተረከቡት አዘዲን ጆውዲ የተባሉ አሠልጣኝ ናቸው። የ48 ዓመቱ ጆውዲ እ.ኤ.አ. በ2001 የአልጄሪያ ብሔራዊ ቡድንን ያሰለጠኑ ሲሆን በሃገራቸው ሊግ ከሚገኙት ክለቦች በተጨማሪ በ2009 የቱኒዚያውን ታላቅ ክለብ ሲኤስ ስፋክሲየን በመምራት ሰፊ ልምድ ያካበቱ አሠልጣኝ ናቸው። በ2004 እና በ2009 የአልጄሪያ የዓመቱ ምርጥ አሠልጣኝ የሚል ማዕረግም አግኝተዋል።

 

የአጨዋወት ፍልስፍና

የኤል ኡልማ አጨዋወት በአብዛኞቹ የሰሜን አፍሪካ ውጤታማ ክለቦች ከምናየው ከክንፍ በሚሻገሩ ኳሶች ላይ የተመሰረተ የጨዋታ ዘይቤ ጋር ተመሳሳይነት አለው። የመስመር አጥቂዎቹ ኢብራሂም ቼኒሂ እና ዋሊድ ደራርጃ ኳሱን ይዘው ድሪብል በማድረግ ወደ መሃል እንዲገቡ ወይንም ለረጅሙ የመሃል አጥቂ ፋሬስ ሃሚቲ የተመጠኑ ኳሶችን እንዲልኩ በማድረግ ግብ ለማስቆጠር ይሞክራሉ። እንደ አብዛኞቹ የሰሜን አፍሪካ ክለቦችም የቆሙ ኳሶችን በአግባቡ ይጠቀማሉ። ኤል ኡልማ በሜዳው እና ከሜዳው ውጪ ሲጫወት ሁለት የተለያየ ቡድን ይመስላል። ከሜዳቸው ውጪ ሲጫወቱ ወደ ኋላ አፈግፍገው በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ወደ ግብ የሚደርሱ ሲሆን በሜዳቸው በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ግን ኳስ በመመስረትና ወደ ተጋጣሚ ሜዳ ክልል ተጭነው በመግባት ፕሬስ እያደረጉ የመጫወት ልምድ አላቸው።

 

ቁልፍ ተጫዋቾች

 

ዋሊድ ደራርጃwalid_derrardja_mcee_2

የትውልድ ቀን፡ መስከረም 18፣ 1990 እ.ኤ.አ

የትውልድ ቦታ፡ ቦውዶአው፣ አልጄሪያ

ዕድሜ፡ 24

የሚጫወትበት ስፍራ፡ አጥቂ፣ የክንፍ አጥቂ

ዋሊድ ደራርጃ ያለ ጥርጥር የወቅቱ የአልጄሪያ ሊግ ምርጥ ተጫዋች ነው። ባለፈው የውድድር ዓመት 7 ግቦችን በማስቆጠር ኤል ኡልማ 4ተኛ ደረጃን ይዞ እንዲያጠናቅቅ ትልቅ አስተዋፅኦ የነበረው ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ የአልጄሪያ ሊግ የኮከብ ተጫዋችነት ፉክክር በ12 ግቦች እየመራ ይገኛል። በአጭር ጊዜ እያሳየ ያለው መሻሻልም ወደፊት ፈረንሳይ ተወልደው ያደጉ ተጫዋቾች የሞሉበትን የአልጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ሰብሮ ይገባል የሚል ግምትን በብዙዎች ዘንድ አሳድሯል።

በአካል ብቃቱ ትልቅ ባይሆንም ፍጥነቱ፣ ተጫዋቾችን አታሎ የማለፍ ብቃቱ እና ከርቀት አክርሮ የሚመታቸው ኳሶች ለተከላካዮች ፈተና ናቸው። ከግብ ጠባቂ ጋር አንድ ለአንድ ሲገናኝ ግቦችን የሚያስቆጥርበት የአጨራረስ ችሎታውም ድንቅ ነው። የኤል ኡልማ የአጥቂ ክፍል ሞተር ስለሆነ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች በዚህ ተጫዋች ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል።

 

ኢብራሂም ቼኒሂ

Chenihi

የትውልድ ቀን፡ ጥር 24፣ 1990 እ.ኤ.አ.

የትውልድ ቦታ፡ ምሲላ፣ አልጄሪያ

ዕድሜ፡ 25

የሚጫወትበት ስፍራ፡ የክንፍ አጥቂ፣ የአጥቂ አማካይ

በግራ ክንፍ እና በአጥቂ አማካይነት መጫወት የሚችለው ቼኒሂ ዘንድሮ ለኤል ኡልማ 5 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። ቼኒሂ እንደ ቡድን ጓደኛው ደራርጃ ፈጣን እና ጥሩ የድሪብሊንግ ችሎታ ያለው ሲሆን ከ16 ከ50 ውጪ አክርሮ በመምታት በሚያስቆጥራቸው ግቦች ይታወቃል። ቼኒሂን ከሌሎች የቡድኑ ተጫዋቾች ለየት የሚያደርገው በ2015ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጉዳት ላይ የነበረውን አብድልሞመን ጃቡ በመተካት አዲስ አበባ ላይ ኢትዮጵያን 2-1 ያሸነፈው የአልጄሪያ ብሄራዊ ቡድን አባል የነበረ መሆኑ ነው።

 

Hamitiፋሬስ ሃሚቲ

የትውልድ ቀን፡ ሰኔ 26፣ 1987 እ.ኤ.አ

የትውልድ ቦታ፡ ብሊዳ፣ አልጄሪያ

ዕድሜ፡ 27

የሚጫወትበት ስፍራ፡ የፊት አጥቂ

 

 

ግዙፉ አጥቂ የአፍሪካ ክለቦች ውድድር ላይ የመሳተፍ ልምድ ካላቸው ጥቂት የቡድኑ ተጫዋቾች ውስጥ አንዱ ነው። በ2010 እስከ ግማሽ ፍፃሜ ድረስ መጓዝ የቻለው የጄኤስ ካባሊዬ ቡድን አባል የነበረ ሲሆን በ2011 ኮንፌዴሬሽንስ ካፕ ላይም ተሰልፎ ተጫውቷል። አምና 13 ግቦችን በማስቆጠር የሊጉ 3ተኛ ግብ አግቢ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ዘንድሮ ደግሞ በ20 ጨዋታዎች 6 ግቦችን በስሙ አስመዝግቧል። ሃሚቲ ከርቀት አክርሮ በመምታትም ሆነ በግል ጥረቱ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ሲያስቆጥር አይታይም። የአጥቂው ዋና መሳሪያ የአየር ላይ ኳሶችን የመጠቀም ችሎታው ሲሆን በቀዳሚነት በግንባር በመግጨት ግቦችን ያስቆጥራል። ከዚህ በተጨማሪም በፔናሊቲ ክልል ውስጥ ግብ ጠባቂ እና ተከላካዮች የሚሰሯቸውን ስህተቶች በመጠቀም የተራረፋ ኳሶችን ያገባል። የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች ሃሚቲ የአየር ኳሶችን እንዳያገኝ ማርክ በማድረግ እና በተከላካይ ክልል አደጋ ላይ ከሚጥሉ አላስፈላጊ አጨዋወቶች በመራቅ ከጨዋታ ውጪ ሊያደርጉት ይችላሉ።

 

ኤል ኡልማ በሜዳው ያለው ጥንካሬ

ኤም ሲ ኤል ኡልማ በሜዳው በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች እጅግ ጠንካራ ነው። አምና በአልጄሪያ ሊግ ማሸነፍ ከቻላቸው 13 ጨዋታዎች ውስጥ 12ቱ በሜዳው ያደረጋቸው መሆናቸው ለዚህ ግልፅ ማሳያ ነው። ከነዚህ ጨዋታዎች ውስጥ በተለይ የፕሪምየር ሊጉን ሻምፒዮን ዩኤስኤም አልጀር 1-0 እንዲሁም የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ሻምፒዮን የሆነውን ኢኤስ ሴቲፍን 2-1 ያሸነፈባቸው ጨዋታዎች ቡድኑ በሜዳው ያለውን ጥንካሬ ያመላክታሉ። በዚህም ምክኒያት በመጀመሪያው ጨዋታ የቅዱስ ጊዮርጊስ ዋነኛ አላማ ሽንፈትን ባለማስተናገድ ባህርዳር ላይ ለሚደረገው የመልስ ጨዋታ ሁኔታዎችን ማመቻቸት መሆን ይኖርበታል።

የዘንድሮ አቋም

በ2014/15 የአልጄሪያ ሊግ ኤል ኡልማ የተዳከመ ይመስላል። ከ20 ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው 7ቱን ብቻ ሲሆን በደረጃው ሰንጠረዥም በ24 ነጥብ 10ኛ ላይ ይገኛል። በስታዴ መሳውድ ዘውጋር ካደረጋቸው 10 ጨዋታዎች ውስጥ 7ቱን በአሸናፊነት መወጣት መቻሉ ግን ዘንድሮም በሜዳው ጠንካራ እንደሆነ ያሳያል።

 

መልካም ዕድል ለቅዱስ ጊዮርጊስ!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *