ኤም ሲ ኤል ኡልማ በባህርዳር የመጀመሪያ ልምምዱን አድርጓል

በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ በመጪው እሁድ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የመልስ ጨዋታውን የሚያደርገው ኤም ሲ ኤል ኡልማ አርብ ዕለት በባህርዳር ብሔራዊ ስታዲየም የመጀመሪያ ልምምዱን ሰርቷል። በልምምዱ ሁሉም የቡድኑ ተጫዋቾች የተሳተፉ ሲሆን በተለይም በአልጄሪያ በተደረገው የመጀመሪያው ጨዋታ ላይ ኤል ኡልማን አሸናፊ ያደረገችውን ጎል በፍፁም ቅጣት ምት ያስቆጠረው ፋሬስ ሃሚቲ ካጋጠመው ጉዳት አገግሞ ወደ ሙሉ ትሬኒንግ መመለሱ ለእንግዳው ክለብ መልካም ዜና ተብሏል።

ኤል ኡልማዎች በአጫጭር ቅብብል ወደ መስመር በመውጣት እና ኳስን ወደ መሃል በማሻማት እንዲሁም ከፍፁም ቅጣት ምት ውጪ ኳስን አክርሮ መምታት ላይ ያተኮረ ልምምድ ሲሰሩ የታዩ ሲሆን ይህም አሠልጣኝ አዘዲን አይት ጆውዲ በእሁዱ ጨዋታ ሊከተሉት ያሰቡትን የጨዋታ ዘይቤ የሚጠቁም ሆኗል።

የአልጄሪያው ክለብ በባህርዳር ስታዲየም ላይ አንዳንድ ቅሬታዎች ያነሳ ሲሆን ከነዚህም መካከል በትራኩ ላይ የሚገኘው የከፍታ ዝላይ ብረት ይነሳልን በማለት ጥያቄ አቅርበዋል። የቅዱስ ጊዮርጊሱ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ አብነት ገብረመስቀልም ከክልሉ የስፖርት ባለስልጣናት ጋር በስታዲየሙ በመዘዋወር ሊስተካከሉ የሚገባቸውን ነገሮች ሲጠቁሙ ውለዋል።

DSC09837

ኤል ኡልማ በሆምላንድ ሆቴል በማረፍ ልምምዳቸውን የሚቀጥሉ ሲሆን በመጪው እሁድ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በሚያደርጉት ጨዋታም በመጀመሪያው ጨዋታ የያዙትን የአንድ ጎል መሪነት ለማስጠበቅ ይጫወታሉ ተብሎ ይጠበቃል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *