አሰልጣኝ ኔይደር ዶስ ሳንቶስ ከቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝነት ተሰናበቱ

ዘንድሮ ቡድኑን በአሰልጣኝነት የተረከቡት ብራዚላዊው አሰልጣኝ ኔይደር ዶ ሳንቶስ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ኃላፊነታቸው ተነስተዋል፡፡ ክለቡ በፌስ ቡክ ገፁ ስንብታቸውን ይፋ ያደረገው እንዲህ ባለ መልኩ ነበር፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ባለው ራዕይ እና በነደፈው እቅድ በአፍሪካ ከሚገኙት ታላላቅ ክለቦች አንዱ ለመሆን እና በውድድር ተሳትፎም በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ስምንት ውስጥ ለመግባት በማሰብ ፋና ወጊ ሆኖ የውጪ ሀገር አሰልጣኝ በማምጣት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ይህንን መሰረት በማድረግ ብራዚላዊው አሰልጣኝ ኔይደር ዶስ ሳንቶስን በመቅጠር በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ከዚህ በፊት ከነበረን ተሳትፎ የላቀ ውጤት ለማምጣት እና የተሻለ ደረጃ እንዲያደርሱን በማሰብ ስምምነት ላይ ደርሰን ቀጥረናቸው እንደነበር አይዘነጋም፡፡

ሆኖም በዘንድሮው የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፏችን በመጀመሪያው ዙር ለመውጣት ተገደናል፡፡አሰልጣኙ ቢጥሩም የክለቡ ስራ አመራር ቦርድ ያስቀመጠውን ግብ ማሳካት ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

በ2007 ዓ.ም እየተደረገ በሚገኘው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮናም እየታየ ያለው እንቅስቃሴ የዋዠቀ እና ተስፋ ሰጪ ሆኖ ባለመገኘቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስራ አመራር ቦርድ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ አሰልጣኝ ኔይደር ዶስ ሳንቶስ ከመጋቢት 11/ 2007 ዓ.ም ጀምሮ እንዲሰናበቱ ወስኗል፡፡

ኔይደር ዶስ ሳንቶስን በመተካትም ምክትል አሰልጣኞቻቸው የነበሩት ፋሲል ተካልኝ እና ዘሪሁን ሸንገታ በዋና አሰልጣኝነት ቅዱስ ጊዮርጊስን የሚያሰለጥኑ ይሆናል፡፡

አሰልጣኝ ኔይደር ዶስ ሳንቶስ በቆይታቸው ወቅት ላደረጉት ጥረት ከልብ እያመሰገንን በሚሄዱበት ሁሉ መልካም እድል እንዲገጥማቸው እንመኛለን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *