ፕሪሚየር ሊግ ፡ ሲዳማ ቡና ወደ መሪነት ተመለሰ

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 15ኛ ሳምንት 3 ጨዋታዎች በክልል ከተሞች ተካሂደው ሲዳማ ቡና የሊጉን መሪነት ከ4 ቀናት በኋላ በድጋሚ ተረክቧል፡፡ በደንጉዛ ደርቢ አርባምንጭ ጣፋጭ ድል ሲያስመዘግብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ሃዋሳ ተጉዞ በሽንፈት ተመልሷል፡፡

ሲዳማ ቡና 2-1 ኤሌክትሪክ

ይርጋለም ላይ ኤሌክትሪክን ያስተናገደው ሲዳማ ቡና 2-1 አሸንፎ ወደ መሪነቱ ተመልሷል፡፡ ኤሌክትሪክ በማናዬ ፋንቱ ግብ 1-0 ቢመራም እንዳለ ከበደ ባለሜዳዎቹን አቻ አደርጎ የመጀመርያው አጋማሽ ሲጠናቀቅ በሁለተኛው አጋማሽ የኤሌክትሪኩ ግብ ጠባቂ አሰግድ አክሊሉ በራሱ ግብ ላይ ከመረብ አሳርፎ ለሲዳማ ቡና ሙሉ ሶት ነጥብ ‹‹ለግሷል››፡፡

ድሉን ተከትሎ ሲዳማ ቡና በ31 ነጥቦች የሊጉን መሪነት ከቅዲስ ጊዮርጊስ በ3 ነጥቦች በልጦ ተረክቧል፡፡

ሀዋሳ ከነማ 2-0 ቅዱስ ጊዮርጊስ

መሪው ቅዱስ ጊዮርጊስን ያስተናገደው ሀዋሳ ከነማ 2-0 አሸንፏል፡፡ በሁለቱ ቡድኖች መካከል የተደረገው የመጀመርያ አጋማሽ ክፍለጊዜ ካለ ግብ የተጠናቀቀ ሲሆን ደስታ ዮሃንስ እና ታፈሰ ሰለሞን በሁለተኛው አጋማሽ ያስቆጠሯቸው ግቦች ሀዋሳ ከነማነን ለደል አብቅቷል፡፡

በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው ሀዋሳ ከነማ 2 ተከታታይ ጨዋታዎችን አሸንፎ ከወራጅ ቀጠናው ወጥቷል፡፡

ወላይታ ድቻ 0-1 አርባምንጭ ከነማ

በዳንጉዛ ደርቢ ለመጀመርያ ጊዜ ሶዶ ላይ የሊግ ጨዋታ ያደረገው ወላይታ ድቻ 1-0 ተሸንፏል፡፡ ከፍተኛ ፉክክር በተደረገበት ጨዋታ ከ10 በላይ የማስጠንቀቅያ ካርዶች እንደተመዘዙ ተነግሯል፡፡

የአርባምንጭ ከነማን የድል ግብ ከመረብ ያሳረፈው ታሪኩ ጎጀሌ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *