በሳምንቱ መዝጊያ መርሐግብር አዳማ ከተማን ከ ወልዋሎ ዓ/ዩ እንዲሁም ነገሌ አርሲን ከምድረ ገነት ሽረ ያገናኙ ጨዋታዎች ዜሮ ለዜሮ በሆነ ውጤት ተጠናቀዋል::

አዳማ ከተማ ከ ወልዋሎ ዓ/ዩ
ቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአሳቴዩ ስታዲየም አዳማ ከተማን ከወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ያገናኘውና ከወራጅ ቀጠናው ስጋት ለመውጣት የተደረገው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ወገኖች የቀዘቀዘ እንቅስቃሴ ያሳዩበት ነበር። ቡድኖቹ ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል በመድረስ ረገድ ደካማ የነበሩ ሲሆን በመጨረሻው የሜዳ ሲሶ ላይ የፈጠራ ብቃት ማነስ በግልጽ ይስተዋልባቸው ነበር። በዚህም ሳቢያ ተጠቃሽ የሚሆን የግብ ሙከራ ሳይመዘገብ የመጀመሪያው አጋማሽ ያለ ግብ በባዶ ለባዶ ውጤት ተጠናቋል።

ከመጀመሪያው አጋማሽ በተለየ ሁለተኛው ክፍለ ጊዜ ሁለቱም ቡድኖች በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ግብ ለመፈለግ የሞከሩበትና ተሻሽሎ የቀረበ ነበር። በዚህም በ58ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ የወልዋሎው ኮንኮኒ ሀፊዝ የሞከረውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ናትናኤል ተፈሬ በግሩም ብቃት ወደ ውጭ ያወጣበት እንዲሁም በ69ኛው ደቂቃ ላይ በአዳማ ከተማ በኩል ዳዋ ሆቴሳ ከረጅም ርቀት አክርሮ የመታው ኳስ በግቡ ቋሚ የተመለሰበት አስቆጪ አጋጣሚዎች ነበሩ። ይሁንና እነዚህ ሙከራዎች ሳይሳኩ ቀርተው ጨዋታው ያለ ግብ በባዶ ለባዶ (0-0) ውጤት ፍጻሜውን አግኝቷል።
ነገሌ አርሲ ከ ምድረገነት ሽረ
በመጀመሪያው አጋማሽ ብልጫ የወሰዱት ነገሌ አርሲዎች በፈጣን አጥቂዎቻቸው በመታገዝ ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል በመጫን ሙከራዎችን አድርገዋል። ገና በጨዋታው መጀመሪያ በ5ኛው ደቂቃ ላይ ኪቲካ ጅማ ያቀበለውን ኳስ ከቤ ብዙነህ አክርሮ ቢመታውም ኢላማውን ሳይጠብቅ በጥቂት በግቡ አግዳሚ ላይ ወጥቶበታል። ፈጣን የማጥቃት ሽግግሮችን በመጠቀም ወደፊት መገስገሳቸውን ቢቀጥሉም የጠራ የግብ ዕድል ባለመፈጠሩ አጋማሹ ያለ ግብ በባዶ ለባዶ ተጠናቋል።

ከእረፍት መልስ ራሳቸውን አሻሽለው ወደ ሜዳ የተመለሱት ምድረ ገነት ሽረዎች የተሻለ እንቅስቃሴ ማሳየት ቢችሉም በሁለቱም ወገኖች በኩል ረዘም ላሉ ደቂቃዎች የጠራ የግብ ሙከራ ሳይመዘገብ ቆይቷል። በ86ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ወልዴ ከሳጥን ውጭ አክርሮ የመታውን አደገኛ ኳስ ግብ ጠባቂው ሪችሞንድ አይ በጥሩ ቅልጥፍና ያደነበት አጋጣሚ የአጋማሹ ብቸኛ ተጠቃሽ የግብ ዕድል ነበር። ከዚያ ውጭ ሌላ አስፈሪ የግብ ስጋት ሳይፈጠር መርሃ-ግብሩ ያለ ምንም ግብ 0-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

