በወልድያ መልካ ቆሌ ስታድየም 9፡00 የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የመጀመርያ አጋማሽ በወልድያ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ተወስዶበታል፡፡
በጨዋታው መጀመርያ አካባቢ ወልድያ የመጀመርያ ሙከራውን በወሰኑ ማዜ አማካኝነት ያደረገ ሲሆን በ20ኛው ደቂቃ ማይክ ሰርጂ የግብ ጠባቂው ኢማኑኤል ፌቮን ከግብ ክልል መውጣት ተመልክቶ ወደ ግብ የላካትን ኳስ ፌቮ አክሽፎበታል፡፡ አዳማዎች የመጀመርያ የግብ ሙከራ ያደረጉት በ28ኛው ደቂቃ ሲሆን ሲሳይ ባንጫ ግብ ከመሆን አድኖታል፡፡ ከዚህ በኋላ በሁለቱም በኩል ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ያልተደረገ ሲሆን የመጀመርያው አጋማሽ መጠናቀቅያ አካባቢ ፍፀም ደስይበለው የአዳማ ተከላካዮችን አልፎ ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጪ በግሩም ሁኔታ የሞከራትን ኳስ ፌቮ አድኖበታል፡፡ የመጀመርያው አጋማሽም ካለምንም ግብ ተጠናቋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ወልድያ በረከትን በሙሃመድ ቀይሮ ጨዋታውን የጀመረ ሲሆን በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች አዳማዎች ወደ ግብ በመድረስ የተሻሉ ነበሩ፡፡ በ47ኛው ደቂቃ የሞከሩት አስደንጋጭ ሙከራ በሲሳይ ባንጫ ሲከሽፍ ከረጅም ርቀት የተሞከረችው ኳስ በግቡ አግዳሚ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥታለች፡፡
በ67ኛው ደቂቃ አሰልጣኝ ሰብስቤ ይባስ ከፍተኛ የተመልካች ተቃውሞ ያስተናገደ የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የዋለው ማይክ ሰርጂን አስወጥተው ተስፋሚካኤልን አስገበተዋል፡፡ ከደቂዎች በኋላ በወልድያ ተከላካዮች በተፈጠረ ስህተት የተገኘውን ጥሩ የግብ ማግባት አጋጣሚ ሲሳይ ባንጫ ከግብ ክልሉ በመውጣት አድኖታል፡፡
በ78ኛው ደቂቃ በሁለቱም በኩል የተጫዋቾች ቅያሪ ሲደረግ ተቃይሮ የገባው ሲሳይ ዴኔቦ እና ፍፁም ደስይበለው ያገኟቸውን ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል፡፡ ጨዋታውም እንደመጀመርያው አጋማሽ ሁሉ በወልድያ የኳስ ቁጥጥር የበላይነትና በአዳማ ጠንካራ መከላከል ያለግብ 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡
የእለቱ ዳኛ በጨዋታው 3 የማስጠንቀቅያ ካርድ ያሳዩ ሲሆን ሁሉም የተሰጡት ለአዳማ ከነማዎች ነው፡፡