በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በተደረገ ብቸኛ ጨዋታ አሰላ ላይ ሙገር ሲሚንቶ ወልድያን አስተናግዶ 1-0 በማሸነፍ ለጊዜውም ቢሆን ከወራጅ ቀጠና ወጥቷል፡፡
የአሰላውን ቡድን ብቸኛዋን የድል ግብ ከመረብ ያሳረፈው አማካዩ እርቅይሁን ተስፋዬ ጨዋታው በተጀመረ ገና በ5ኛው ደቂቃ ነው፡፡ ሙገር ይህንን ጨዋታ በማሸነፉ በ17 ነጥቦች ኤሌክትሪክን በግብ ልዩነት በልጦ 11ኛ ላይ ሲቀመጥ በውድድር ዘመኑ 1 ጨዋታ ብቻ ያሸነፈው ወልድያ በ6 ነጥቦች የመጨረሻውን ደረጃ ይዟል፡፡
ሊጉ እስካሁን የ17 ሳምንት ጨዋታዎችን ያስተናገደ ሲሆን ደደቢት በአፍሪካ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ተሳትፎው ምክንያት 2 ጨዋታዎች (ከሀዋሳ ከነማ እና ወላይታ ድቻ) አምልጠውታል፡፡ አዳማ እና ሀዋሳ ከነማም እርስ በእርስ የሚያደርጉት ጨዋታ ሌላው ተስተካካይ ግጥሚያ ነው፡፡