በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 18ኛ ሳምንት ጨዋታ ወደ ጎንደር ያቀናው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዳሽን ቢራን 2ለ1 ማሸነፍ ችሏል፡፡ ለንግድ ባንክ ጎሎቹን ሲሳይ ቶሊ እና ኤፍሬም አሻሞ በስማቸው አስመዝግበዋል፡፡ ለዳሽን ቢራ ከባዶ መሸነፍ ያዳነቻቸውን ግብ መድሃኔ ታደሰ አስቆጥሯል፡፡ ድሉን ተከትሎ ንግድ ባንክ ሶስተኛነቱን በ31 ነጥብ ማስጠበቅ ችሏል፡፡ የሁለተኛው ዙር ከተጀመረ ጀምሮም ያሉትን ሁሉንም ጨዋታዎች ያሸነፈ ብቸኛው ቡድን ነው፡፡ በውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው ዳሽን ቢራ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከነማ ኢትዮጵያ ቡናን በተሾመ ታደሰ ብቸኛ ጎል 1ለ0 ማሸነፍ ችሏል፡፡ ተሾመ ግቧን በ27ኛው ደቂቃ ማስቆጠር ችሏል፡፡ ውጤቱ ኢትዮጵያ ቡናን አጣብቂኝ ውስጥ ከቷል፡፡ ድሉን ተከትሎ አርባምንጭ 5ተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ኢትዮጵያ ቡና 4ተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡