የጨዋታ ሪፖርት – ወልድያ 2-1 ሀዋሳ ከነማ

መሃመድ አህመድ ከወልድያ

 

በመልካ ቆሌ ስታድየም 9፡00 ላይ በተካሄደው 18ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ በወራጅ ቀጠናው ውስጥ ያሉት ወልድያዎች ሌላው በቀጠናው ውስጥ ያለው ሀዋሳ ከነማን በማሸነፍ ነጥቡን ወደ 9 ከፍ አድርጓል፡፡

በውጤት መጥፋት ምክንያት የተመልካች ቁጥር ቀንሶ በታየበት ጨዋታ ወልድያዎች የመጀመርያ የግብ ማግባት አጋጣሚ በ8ኛው ደቂ ቢያገኙም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፡፡ በመጀመርያው አጋማሽ ሀዋሳ ከነማዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫን የያዙ ሲሆን ወልድያዎች በመልሶ ማጥቃት እና ከቆሙ ኳሶች አደጋ ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡

በ25ኛው ደቂቃ ወልድያዎች ያገኙትን ቅጣት ምት ሳሙኤል ደግፌ ወደ መሃል አሻምቶ የሀዋሳ ተከላካዮች ከግብ ክልላቸው በሚገባ ማራቅ ባለመቻላቸው ፍሬው ብርሃን ኳሷን አግኝቷት ወደ ግብነት ቀይሯታል፡፡ ወልድያ በ33ኛው ደቂቃ በአብይ በየነ አማካኝነት በድጋሚ ግብ ቢያስቆጠርም ረዳት ዳኛው ከጨዋታ ውጪ ምልክት በማሳየታቸው ሳይፀድቅ ቀርቷል፡፡

ከግቧ መቆጠር በኋላ ሀዋሳ ከነማ ጫና ፈጥሮ ለመንቀሳቀስ የሞከረ ሲሆን በ40ኛው ደቂቃ ላይ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ የአቻነት ግብ ማስቆጠር ችለዋል፡፡ የመጀመርያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለጊዜም 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

ከእረፍት መልስ ሀዋሳዎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጫናቸውን አጠናክረው ተጫውተዋል፡፡ በ50ኛው ደቂቃ ሲሳይ ባንጫ የፈጠረውን ስህተት ተጠቅመው ሀዋሳዎች ለግብ የቀረበ አጋጣሚ ቢያገኙም በቶክ ጀምስ ጥረት ግብ ሳይሆን ቀርቷል፡፡

ወልድያዎች በሁለተኛው አጋማሽም እንደመጀመርያው ሁሉ አፈግፍገው በመጫወት በመልሶ ማጥቃት ወደ ግብ ለመድረስ የሞከሩ ሲሆን አብይ በየነ በዚህ ሂደት የተገኘቸውን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮ በግቡ ቋሚ ለጥቂት ወጥታበታለች፡፡

በ80ኛው ደቂቃ በ2ኛው አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አጥቂው ፍፁም ደስይበለው ሳሙኤል ደግፌ ከማእዘን ምት ሸገረውን ኳስ በግንባሩ በመግጨት ግብ አስቆጥሯል፡፡

ጨዋታው በወልድያ መሪነት ቀጥሎ በዳኛ ውሳኔ ቅሬታ ውስት የገቡ የወልድያ ደጋፊዎች መጠነኛ ረብሻ ቢያስነሱም በፀጥታ ኃይሎች እና በወልድያ ተጫዋቾች ትብብር በቶሎ ረግቧል፡፡ ጨዋታውም በወልድያ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

በጨዋታው የእለቱ አልቢትር ለሁለቱም ቡድኖች አንድ አንድ ቢጫ ካርድ አሳይተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *