ፕሪሚየር ሊግ ፡ ኤሌክትሪክ ከሙገር አቻ ሲለያዩ አዳማ ድቻን አሸነፈ

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ወልድያ እና አዳማ ከነማ ድል ሲቀናቸው ኤሌክትሪክ ከሙገር በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

መልካቆሌ ላይ ሀዋሳ ከነማን ያስተናገደው ወልድያ 2-1 በማሸነፍ የውድድር ዘመኑን 2ኛ ድል አስመዝግቧል፡፡ ወለድያዎች አሸናፊ የሆኑበትን ግብ ያስቆጠሩት ፍሬው ብርሃን እና ፍፁም ደስይበለው ናቸው፡፡

አዳማ ላይ ወላይታ ድቻን ያስተናገደው አዳማ ከነማ 1-0 በማሸነፍ ደረጃውን ኣሻሽሏል፡፡ የአዳማ ከነማን ግብ ከመረብ ያሳረፈው አጥቂው በረከት አዲሱ በመጀመርያው አጋማሽ ነው፡፡

አዲስ አበባ ስታድየም ላይ በመውረድ ስጋት ውስጥ የሚገኙት ኤሌክትሪክ እና ሙገር ሲሚንቶ ባደረጉት ጨዋታ ሳይሸናነፉ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ግብ በማስቆጠር ቅድሚያውን የያዙት ሙገሮች ሲሆኑ ጋናዊው ጌድዮን አካክፖ በግሩም ሁኔታ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ኤሌክትሪኮች በሁለተኛው አጋማሽ ጫና ፈጥረው መንቀሳቀስ የቻሉ ሲሆን አማረ በቀለ ከመስመር ያሻገረውን ኳስ የሙገሩ ግብ ጠባቂ አቤል ማሞ በአግባቡ ባለመቆጣጠሩ ግብ ሆናለች፡፡

ከጨዋታው በኋላ የኤሌክትሪኩ አሰልጣኝ አጥናፉ አለሙ የእለቱን ዳኛ ኮንነዋል፡፡ ‹‹ በዛሬው እለት የገጠመን ዋነኛው ፈተና ዳኛው ነው፡፡ ተጫዋቾቼ ተረጋግተው እንዳይጫወቱ በየደቂቃው ፊሽካ ሲነፋ ነበር፡፡ ከዚህ ውጪ የቡድኔ እንቅስቃሴ መልካም ነበር፡፡ ጠንክረን በመስራት ወደ አሸናፊነት እንመለሳለን፡፡ ›› ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ አያይዘውም የመባረር ስጋት እንደሌለባቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ ቡድናችን የመውረድ ስጋት የለበትም፡፡ በቀሪ ጨዋታዎች ውጤት አምጥተን ደረጃችንን እናሻሽላለን፡፡ ስለዚህ የመባረር ስጋት አይሰማኝም፡፡ እሰናበታለሁ ብዬ እቅልፌን አጥቼ የማድር ሰው አይደለሁም›› ሲሉ ሀሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡

የሙገሩ አሰልጣኝ ግርማ ኃ/ዮሃንስ በበኩላቸው በውጤቱ እንዳልተከፉ ተናግረዋል፡፡

‹‹ አቻ አስበን አልመጣንም፡፡ ነገር ግን ኤሌክትሪክ ጫና ፈጥሮ ከመጫወቱ አንፃር የአቻ ውጤቱ ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በዳኛው ላይ ቅሬታ የለብኝም፡፡ ምክንያቱም በጥቃቅን ነገሮች ፊሽካ ከመንፋት ውጪ ጉልህ ስህተት አልነበረም፡፡ ›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *