በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 19ኛ ሳምንት ጨዋታ ዛረ 11፡30 ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አርባምንጭ ከነማን አስተናግዶ 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል፡፡
ናይጄርያዊው ግዙፍ አጥቂ ፊሊፕ ዳውዚ በ14ኛው እና 64ኛው ደቂ ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች የኢትጵያ ንግድ ባንክ የጨዋታውን 2/3ኛ ክፍለጊዜ በ 2-0 መሪነት ቢዘልቅም አማኑኤል ጎበና በ72ኛው እና ተሸመ ታደሰ በ85ኛው ደቂቃ ባስቆጠሯቸው ግቦች አርባምንጮች ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል፡፡
የአቻ ውጤቱን ተከትሎ ንግድ ባንክ ከመሪዎቹ ለመጠጋት የነበረውን እድል ሲያመክን 5 ተከታታይ ጨዋታዎችን ያሸነፈው ባንክን ነጥብ ያስጣለው አርባምንጭ ደረጃውን ወደ 6 ከፍ አድርጓል፡፡
ከጨዋው በኋላ የንግድ ባንኩ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ስህተቶች ዋጋ እንዳስከፈላቸው ተናግረዋል፡፡
‹‹ 3 ነጥብ ይዘን ለመውጣት ጥረት አድርገናል፡፡ ነገር ግን በመጨረሻዎቹ 20 ደቂቃዎች የፈጠርናቸው የአቋቋም ስህተቶች ግብ እንዲቆጠርብን አድርጓል፡፡ ተጫዋቾቼ ጉጉት ከፍተኛ መሆንም ሙሉ አቅማቸውን አውጥተው እንዳጠቀሙ አድርጓቸዋል፡፡ የተጋጣሚችን መጫወት ፍላጎት ጥሩ ነበር፣ በየቦታቸው የተሰለፉት ተጫዋቾችም ጥሩ ነበሩ ፣ ደጋፊዎቻቸውም በሚገባ አነሳስተዋቸዋል፡፡ ስለዚህ ውጤቱ ለሁለታችንም ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
አርባምንጩ አሰልጣኝ አለማየሁ አባይነህ በበኩላቸው እስከመጨረሻው መታገላቸው ውጤት እንዳስገኘላቸው ገልፀዋል፡፡
‹‹ በውጤቱ ደስተኛ ነኝ፡፡ በጨዋታ ብንበልጥም የያገኙትን አጋጣሚ ወደ ግብ በመለወጥ ከኛ የተሻሉ ነበሩ፡፡ ነገር ግን እስከ መጨረሻው በመታገላችን ግቦች አስቆጥረን አቻ መውጣት ችለናል፡፡ መሪዎቹ ከኛ ባለመራቃቸውና ከባባድ ጨዋታዎችን ከወዲሁ በመጫወታችን የተሻለ ስፍራ ላይ ሆነን ሊጉን እናጠናቅቃለን ብለን እናስባለን፡፡›› ብለዋል፡፡