አዳማ ከተማ የሦስት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቋል

በርካታ ዝውውሮችን ሲያከናውን የሰነበተው አዳማ ከተማ የሙከራ ዕድል ሰጥቷቸው የነበሩትን የቀድሞው የተስፋ ቡድን ተጫዋቾቹን እና ከዚህ ቀደም ለማስፈረም ተስማምቶ የነበረውን ተጫዋች በይፋ አስፈረመ፡፡

ከሳምንታት በፊት ወደ ቡድኑ ለመቀላቀል ተስማምቶ የነበረው አቡበከር ወንድሙ ወደ አዳማ ያደረገውን ዝውውር አጠናቐል። የውድድር ዓመቱን በአዲስ አበባ ከተማ ያሳለፈው የመስመር አጥቂው እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2014 ድረስ በአዲስ አበባ ከተማ ውል የነበረው ቢሆንም በስምምነት ከመዲናይቱ ክለብ ጋር ተለያይቶ ቀድሞ ስምምነት የፈፀመበትን አዳማ ከተማን በሁለት ዓመት ውል ተቀላቅሏል።

የመስመር አጥቂው ጅብሪል አህመድ ሌላው አዳማን የተቀላቀለ ተጫዋች ሆኗል፡፡ እግርኳስን በአዳማ ከ17 ዓመት በታች ቡድን በመጫወት የጀመረው ይህ ተጫዋች በመቀጠል ወደ ዱከም ከተማ ከተማ እንዲሁም ያለፉትን አራት ዓመታት ደግሞ በገላን ከተማ በመጫወት ካሳለፈ በኋላ የልጅነት ክለቡ አዳማ ከተማ የሰጠውን የሙከራ ዕድል በአግባቡ በመወጣቱ ፊርማውን አኑሯል፡፡

ሌላኛው የሙከራ ዕድሉን በመጠቀም ፊርማውን ያኖረው ዘካሪያስ ከበደ ነው፡፡ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ዘካሪያስ ከዚህ ቀደም በአዳማ ከተማ ከ17 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ በመጫወት ያሳለፈ ሲሆን በመቀጠል ለሪፍት ቫሊ ኮሌጅ (የቀድሞው የአንደኛ ሊግ ተሳታፊ ቡድን) ፣ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ከ20 ዓመት በታች እና ዋናው ቡድን እንዲሁም ያለፉትን ሦስት ዓመታት በለገጣፎ ለገዳዲ ከተጫወተ በኋላ እንደ ጅብሪል ሁሉ አሳዳጊ ክለቡን ተቀላቅሏል፡፡