ፕሪሚየር ሊግ: ሙገር ለመጀመርያ ጊዜ ሊወርድ ተቃርቧል

ዛሬ በተካሄዱ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ደደቢት ፣ ኤሌክትሪክ እና ኢትዮጵያ ቡና ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል፡፡

አሰላ ላይ ወላይታ ድቻን ያስተናገደው ሙገር ሲሚንቶ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቶ በፕሪሚየር ሊጉ የመቆየት ተስፋውን አጨልሟል፡፡ ሙገሮች በመጀመርያው በቀጣዩ የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታ ኤሌክትሪክ ወደ ሶዶ ተጉዞ 1 ነጥብ ማግኘት ከቻለ በ1991 ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ካደገ ወዲህ ወደ ታችኛው ዲቪዥን ወርዶ የማያውቀው ሙገር ሲሚንቶ ከሊጉ ይሰናበታል፡፡

ወደ አርባምንጭ ያቀናው ደደቢት አርባምንጭ ከነማን 3-0 አሸንፎ 2ኛ ደረጃን ከአዳማ ከነማ ተረክቧል፡፡

ናይጄርያዊው አጥቂ ሳሙኤል ሳኑሚ በ15ኛው ፣ 47ኛው እና 90ኛው ደቂቃ ባስቆጠራቸው 3 ግቦች የውድድር ዘመኑ 2ኛ ሐት-ትሪኩን ሲሰራ የግብ መጠኑንም 22 በማድረስ የከፍተኛ ግብ አግቢነቱን በ22 ግቦች መምራቱን ቀጥሏል፡፡

ፊሊፕ ዳዊዚ ከሳሙኤል ሳኑሚ በ4 ግቦች ርቆ የሚገኝ በመሆኑ የደደቢቱ አጥቂ የኮከብ ግብ አግቢነቱን ክብር የወሰደ የመጀመርያው የውጪ ዜጋ ለመሆን ከጫፍ ደርሷል፡፡ የዮርዳኖስ አባይን 14 አመት የቆየ የ24 ግብ በአንድ የውድድር ዘመን የማስቆጠር ሪኮርድ ለመስበር ግን በመጨረሻው ሳምንት የቀድሞ ክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ሌላ ሐት-ትሪክ መስራት ይጠበቅበታል፡፡

በአዲስ አበባ ስታድየም ሲዳማ ቡናን ያስተናገደው ኢትዮጵያ ቡና 3-0 አሸንፏል፡፡ ለበርካታ ሳምንታት የከፍተኛ ግብ አግቢነት ሰንጠረዡን ሲመራ የነበረው ቢንያም አሰፋ በ8ኛው እና 35ኛው ደቂቃ 2 ግቦች ሲያስቆጥር አስቻለው ግርማ በ81ኛው ደቂቃ ተጨማሪዋን ግብ ከመረብ አሳረፏል፡፡

ኢትዮጵያ ቡና ከተደጋጋሚ ሽንፈቶች በኋላ ሁለተኛ ተከታታይ ድሉን ሲያስመዘግብ ሲዳማ ቡና የሁለተኛው ዙር መጥፎ ጉዞውን ቀጥሎበታል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *