ኤሌክትሪክ በውድድር ዘመኑ ከፍተኛ ድል በሊጉ የመቆየት ተስፋውን አለምልሟል

 

አዲስ አበባ ላይ ሀዋሳ ከነማን ያስተናገደው ኤሌክትሪክ 6-0 በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፍ በሊጉ የመቆየት ተስፋውን አለምልሟል፡፡ በ33ኛው ደቂቃ የሃዋሳው ግብ ጠባቂ ክብረአብ ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጪ ፍቅረማርያም ላይ ጥፋት በመስራቱ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ የተወገደ ሲሆን የተገኘውን ቅጣት ምት ሄይቲያዊው አማካይ ሶውረን ኦልሪስ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብነት ቀይሯታል፡፡ የጨዋታው የመጀመርያ አጋማሽ ተረጠናቆ በተሰጠው ተጨማሪ ደቂቃ ናይጄርያዊው አጥቂ ፒተር ኑዋድኬ ከፍቅረማርያም የተሻገረለትን ኳስ በቀላሉ ወደ ግብነት ቀይሮ ኤሌክትሪክ በ 2-0 መሪነት እረፍት እንዲወጣ አስችሏል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ኤሌክትሪኮች ተሸለው የቀረቡ ሲሆን በ10 ተጫዋቾች ለመጫወት የተገደዱት ሀዋሳዎች ፍፁም ተዳክመው ቀርበዋል፡፡

ራምኬል ሎክ በ57 እና 66ኛው ደቂቃ አከታትሎ ሁለት ግቦች ሲያስቆጥር ማናዬ ፋንቱ ተቀይሮ የገባው በሃይሉ ተሸገር ደግሞ በ68ኛው ደቂቃ የኤሌክትሪክን ግቦች ከመረብ አሳርፈዋል፡፡

ከጨዋታው በኋላ አስተያየታቸውን የሰጡት ብርሃኑ ባዩ የተጫዋቾቻቸው ትጋት ለድል እንዳበቃቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ በዛሬው ጨዋታ ተጫዋቾቼ ለቡድኑ ካላቸው አቅም በላይ በመልፋታቸው ይህንን ውጤት ይዘን እንድንወጣ አስችሎናል፡፡ ታሪካዊው ክለብ በውጤት ማጣት ውስጥ በመሆኑና በኛ ጊዜ እንዳይወርድ በኛ እና ተጫዋቾቹ መካከል ውይይት አድርገን በጥሩ ተነሳሽነት እና አእምሮ ዝግጁነት ወደ ሜዳ ገብተናል፡፡ ያሰብነውንም ሜዳ ላይ ተግብረን ወጥተናል፡፡ ››

‹‹ ሃዋሳ ከደደቢት ያደረገውን ጨዋታ ተመልክተን ተዘጋጅተናል፡፡ ድክመታቸው ምን እደሆነ አውቀን ገብተናል፡፡ በታፈሰ ሰለሞን ዙርያ ቡድኑ በመገንባቱም የሱ አለመኖር ለኛ ጠቅሞናል፡፡ ››

‹‹ በጨዋታው የቁጥር ብልጫ በርካታ ግቦች እንድናስቆጥር እገዛ አድርጎልናል፡፡ ሀዋሳ ከነማ የመጣው ሊያሸንፈን ነው፡፡ ከደደቢት ጋር እንኳን እንደዛሬው አልተንቀሳቀሱም፡፡ ሜዳ ላይ የማሸነፍ ፍላጎታቸው ከፍተኛ ነበር፡፡ ›› ብለዋል፡፡

የሀዋሳ ከነማው ውበቱ አባተ በበኩላቸው የግቡ መጠን የቡድኑን እንቅስቃሴ እንደማይመጥን ተናግረዋል፡፡

‹‹ 3 ተጫዋቾች ከቋሚ አሰላለፍ ውጪ ሆነው ነው ጨዋታውን የጀመርነው፡፡ በቶሎ ግብ ጠባቂያችን በቀይ ካርድ መሰናበቱና ተክቶት የገባውግብ ጠባቂ ለጨዋታው ብቁ ያልነበረ መሆኑ ጨዋታው ከቁጥጥራችን ውጪ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ››

‹‹ መሸነፍ ይገባናል፡፡ ነገር ግን የግብ መጠኑ ያደረግነውን እንቅስቃሴ አይመጥንም፡፡ ለ70 ደቂቃዎች በጎዶሎ ተጫዋቾች በመጫወታችን ድሉ ቢገባቸውም አብዛኛዎቹ ግቦች የተቆጠሩብን በራሳችን ስህተት ነው፡፡ ››

‹‹ ዛሬ የተጫወትነው ከአቅም በላይ ነው፡፡ ከአቅም በታች ተጫውተን እነሱን ለመጥቀም ብንፈልግ በ1 እና 2 ግቦች ልዩነት መሸነፍ እንችል ነበር፡፡ ህሊናችንን ሽጠን 6 ግቦች እንዲቆጠርብን አናደርግም፡፡ መጥፎ አቋም ላይ ከተገኘህ በርካታ ግብ ማስተናገድ የእግርኳስ አንዱ ባህርይ ነው፡፡ ›› ብለዋል፡፡

ኤሌክትሪክ የ6-0 ድሉን ተከትሎ በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በሰፊ የግብ ለክዩነት በማሸነፍ ቀዳሚው ክለብ መሆን ሲችል የነበረበትን 12 የግብ እዳ ወደ 6 ዝቅ ማድረግም ችሏል፡፡ ኤሌክትሪክ በሊጉ መቆየቱን ለማረጋገጥ በመጨረሻው ጨዋታ ከሶዶ 1 ነጥብ ይዞ መመለስ በቂው ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *