የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በወዳጅነት ጨዋታ ከዛምቢያ እና ታንዛኒያ ጋር እንደሚያደርግ ተነግሯል፡፡ ዋሊያዎቹ ጋቦን ለምታዘጋጀው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በምድብ ማጣሪያው ሰኔ 7 ከሌሴቶ ጋር ለሚደርገው ጨዋታ የሚጠቅሙ የተባሉ ሁለት የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች የሚያደርግ ይሆናል፡፡ ዋሊያዎቹ ከ2012 የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ዛምቢያ ጋር ከሰኔ 1-4 ባሉት ቀናት የሚጫወቱ ይሆናል፡፡ የታንዛኒያ ብሄራዊ ቡድን ከግንቦት 27 ጀምሮ አዲስ አበባ ላይ ልምምድ ይሰራል፡፡ ታይፋ ስታርስ በሚል ስም የሚታወቁት ታንዛኒያዎች ከግብፅ ጋር ላለባቸው አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ጨዋታ ከኢትዮጵያ ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ተነግሯል፡፡ ታንዛኒያ እና ዛምቢያ አሁን እየተደረገ ባለው የኮሳፋ ዋንጫ ላይ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ በቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ማርት ኖይ የሚሰለጥነው የታንዛኒያ ብሄራዊ ቡድን በኮሳፋ ዋንጫ ከምድቡ ማለፍ አልቻለም፡፡ በሆነር ጃንዛ የሚመሩት ቺፖሎፖሎዎቹ በሩብ ፍፃሜ በናሚቢያ ተሸንፈው ከውድድሩ ውጪ ሆነዋል፡፡ ኢትዮጵያ ምድብ ውስጥ ያሉት ሲሸልስ እና ሌሴቶ በኮሳፋ ዋንጫ ከምድባቸው ማለፍ አልቻሉም፡፡ ሁለቱ የወዳጅነት ጨዋታዎች ኢትዮጵያን እንደሚጠቅሙ ታምኖበታል፡፡
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ጁነዲ ባሻ ዛሬ በግል የትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ ፌድሬሽኑ የወዳጅነት ጨዋታ ለዋሊያዎቹ ለማዘጋጀት እየሰራ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
‹‹ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለብሔራዊ ቡድኑ የቻን 2016 እና የአፍሪካ ዋንጫ 2017 የማጣሪያ ጨዋታዎች ዝግጅት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ተዘጋጅቷል:: የወዳጅነት ጨዋታዎችን ለማድረግም ከስምምነት ደርሰናል:: ››