ሊጠናቀቅ አንድ ጨዋታ በቀረበት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የኮኮብ ግብ አግቢነትን በ22 ጎሎች አየመራ የሚገኘው ናይጄሪያዊው የመስመር አማካይ እና አጥቂ ሳሙኤል ሳኑሚ ነው፡፡ በ2006 የክረምቱ የዝውውር መስኮትን ተከትሎ ደደቢትን የተቀላቀለው ሳኑሚ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለቅዱስ ጊዮርጊስ እና መብራት ሃይል ተጫውቶ አሳልፏል፡፡ በ2006 ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የሊጉ ቻምፒዮን ነበር፡፡ ሳኑሚ ዘንድሮ ስላሳየቀው ብቃቱ እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
ስለጠንካራ ጎኑ
ሰዎች የአንተ ጠንካራ ጎን ያለህ ፍጥነት ነው ይሉኛል፡፡ አዎ ፈጣን ነኝ ፍጥነቴ ግቦችን እንዳስቆጥር ረድቶኛል፡፡ ጠንክሬ ልምምድ መስራቴ ነው አሁን ላስቆጠርኩት የግብ መጠን አድርሶኛል፡፡ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ጠንክሬ እንድሰራ ይመክረኝ ነበር፡፡ ከአሰልጣኜ የሚሰጠኝን ምክር በአግባቡ መከተሌ ጠቅሞኛል፡፡
ስለአቆጠራቸው ግቦች መጠን
22 የሊግ ጎል ማስቆጠሬ እኔን በጣም አስገርሞኛል፡፡ ያን ያህል የግብ መጠን አስቆጥራለው ብዬ ፈፅሞ አላሰብኩም፡፡ በርግጥ ቅዱስ ጊዮርጊስን ለቅቄ ደደቢት ስገባ ግቦችን እንደማስቆጥር ጥርጥር አልነበረኝም፡፡ ችሎታው እናዳለኝ ሰዎች ይነግሩኛል በራስ መተማመኔን እንድጨምር አድርጎኛል፡፡
ስለዮርዳኖስ አባይ የ24 ጎል ሪከርድ
የማይቻል ነገር የለም፡፡ ግብ ማስቆጠር ስራዬ ነው፡፡ ስለዚህም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ስንጋጠም ያንን ስራዬን እቀጥላለው፡፡ በእግርኳስ የሚከብድ ነገር የለም፡፡ አውቃለው ሮበርት ኦዶንካራ በሊጉ አለ የሚባል ምርጥ ግብ ጠባቂ ነው፡፡ ነገር ግን ሮበርትን አልፈራውም እሱ ላይም ግብ እቆጥራለው፡፡ በነገራችን ላይ ሮበርት ጥሩ ጓደኛዬ ነው እራሴን እዳሻሽል ምክሮችን ይለግሰኛል፡፡
ስለፊሊፕ ዳውዝ
ፊሊፕ ጥሩ አጥቂ ነው፡፡ ለኔ ወንድሜ እና ጓደኛዬ ነው፡፡ ከፊሊፕ እና ከቢኒያም ጋር የነበረን ፉክክር አሁን ላለሁበት የገብ መጠን አድርሶኛል፡፡