በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ24ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሃግብር በሆነውና ኢትዮጵያ ቡናን ከወልዲያ ጋር ባገናኘው የአዲስአበባ ስታዲየም ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና 2ለ1 በሆነ በማሸነፍ ከተከታታይ ነጥብ መጣሎች በኃላ ወደ ድል ተመልሷል፡፡
በጨዋታው ባለሜዳው ኢትዮጵያ ቡና ባሳለፍነው ሳምንት ቅዳሜ በሸገር ደርቢ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር 1አቻ ከተለያየው ቡድን ስብስብ ውስጥ መስኡድ መሀመድን ከአንድ ጨዋታ ቅጣት በተመለሰው ጋቶች ፓኖም እንዲሁም እያሱ ታምሩን በካሜሮናዊው የመስመር አጥቂ ያቡን ዊልያም ብቻ ተክተው ጨዋታው በተመሳሳይ የ4-3-3 ቅርፅ መጀመር ችለዋል፡፡
በአንጻሩ እንግዳዎቹ ወልዲያዎች በተለመደው የ4-4-2 ቅርፅ ተከላካይ መስመር ላይ ከአዳሙ መሀመድ ጋር በፈጠሩት ጠንካራ የመሀል ተከላካይ ጥምረት የሚታወቀውን ያሬድ ዘውድነህን ወደ ቀኝ ተከላካይ ስፍራ አምጥተው በእሱ ምትክ አለማየሁ ግርማን በመሀል ተከላካይነት መጠቀም ሲችሉ አጥቂ ስፍራ ላይ አንዱአለም ንጉሴንና ጫላ ድሪባን ማጣመር ችለዋል፡፡
ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታ ክፍለ ጊዜ ገና በማለዳው ነበር ግብ መቆጠር የቻለው፡፡በ6ኛው ደቂቃ ላይ በወልዲያ ከተሞች የግብ ክልል የግራ ጠርዝ ላይ ያሬድ ዘውድነህ በአስቻለው ግርማ ላይ በሰራው ጥፋት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ጋቶች ፓኖም ወደ ግብነት ቀይሮቡድኑን መሪ ማድረግ ቻለ፡፡
በደቂቃዎች ልዮነት ጋቶች ፓኖም የግብ ልዮነቱን ሊያሰፋ የሚችልበትን አጋጣሚ ከረጅም ርቀት አክርሮ በመምታት የሞከራት ኳስ ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ ልትወጣበት ችላለች፡፡
ጨዋታው ከተጀመረ 12 ያክል ደቂቃዎች በሞላበት ወቅት የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ባሳለፍነው ሳምንቱ በክለቡ አመራሮች ለክለቡ ደጋፊዎች ባበረከቱት የ12 ቁጥር መለያን መታሰቢያ በማድረግ በሜዳው ውስጥ ማራኪ የአደጋገፍ ትእይንትን ማሳየት ችለዋል፡፡
በሁለቱም ቡድኖች በኩል አልፎ አልፎ ብልጭ ድርግም ከሚሉ የጨዋታ እንቅስቃሴዎች በቀር ያን ያህል የመጀመሪያው አጋማሽ እንቅስቃሴ ሳቢ አልነበረም፡፡
አሰልጣኝ ንጎሴ ደስታ በ4-4-2 የተጫዋቾች አደራደር ከአማካዮቹ በግራና ቀኝ የሚገኙት ሁለቱ የመስመር አማካዮች የሆኑት ያሬድ ሀሰንና ሀብታሙሸዋለም በጥልቀት ወደ መሀል እየገቡ በመጫወት የኢትዮጵያ ቡናን የመሀል ሜዳ የበላይነትን ለመውሰድ ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ በአመዛኙም ወልዲያዎች በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ በራሳቸው የግብ ክልል ወደ ኃላ አፈግፍገው ሲከላከሉ ተስተውሏል፡፡
ኢትዮጵያ ቡናዎች በ16ኛውና በ35ኛው ደቂቃ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ያገኟቸውን ሁለት ወርቃማ የግብ ማግባት አጋጣሚዎች አብዱልከሪም መሀመድና ሳሙኤል ሳኑሚ ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል፡፡
በዚሁ በመጀመሪያው አጋማሽ የኢትዮጵያ ቡናው የቀኝ መስመር ተከላካይ የሆነው አብዱልከሪም መሀመድ ባጋጠመው ጉዳት የተነሳ በአስናቀ ሞገስ ተቀይሮ ከሜዳ ሊወጣ ችሏል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው በተለየ ሁለቱ የወልዲያ ከተማ የመስመር አማካዮች በሜዳው የጎንዮሽ ቁመት አስፍተው በመጫወት በቶሎ ቶሎ ኳሶችን ወደ ሳጥን ውስጥ ለመጣል ሲሞክሩ ተስተውሏል፡፡
ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በተለይም በ50ኛው እና በ51ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው በወልዲያዎች በኩል ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ያሬድ ሀሰን ከቀኝ መስመር ያሻማቸው አደጋ ፈጣሪ ኳሶችን አንዱአለም ንጎሴና ሀብታሙ ሸዋለም አልተጠቀሙባቸውም እንጂ ወልዲያን ወደ ጨዋታው መመለስ የሚችሉ አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡
ወልዲያዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ማንሰራራት ባሳዩበት የሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያው ደቂቃዎች ኢትዮጵያ በ52ኛው ደቂቃ በፈጣን መልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ አክሊሉ ዋለልኝ ከኢትዮጵያ ቡና የግብ ክልል በረጅሙ ያሳለፈለትን ኳስ ሳሙኤል ሳኑሚ ሁለቱን የወልዲያ ከተማ የመሀል ተከላካዮችን በፍጥነት በማለፍ ኤሌክሪም ቤሌንጌ መረብ ላይ ግሩም ግብን አስቆጥሮ የወልዲያዎችንን መነቃቃት ያከሰመችውን ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡
ከግቧ መቆጠር በኃላ ኢትዮጵያ ቡናዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ ይበልጥ ጫና ፈጥረው መጫወት ቢችሉም ከመሀል ሜዳ ብልጫ በዘለለ ይህ ነው የሚባል የግብ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም፡፡ በአንጻሩ ወልዲያዎች ከመጀመሪያው በተሻለ በጥሩ መንቀሳቀስ ቢችሉም ውጤቱን መቀልበስ ሳይችሉ ቀርተዋል ሆኖም ግን በ93ተኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ሙሉጌታ ረጋሳ ከቀኝ መስመር የግሉን ጥረት ተጠቅሞ ወደ መሀል ሰብሮ ከገባ በኃላ በግሩም ሆኔታ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት ከባዶ መሸነፍ ያዳነቻቸውን ግብ ለማስቆጠር ችሏል፡፡
በዚህም ውጤት መሠረት ኢትዮጵያ ቡና ነጥቡን ወደ 39 በማሳደግ በ4ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል፡፡
ከጨዋታው በኃላ የሁለቱም ቡድኖች አሰልጣኝ በሚከተለው መልኩ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ገዛኸኝ ከተማ – ኢትዮጵያ ቡና
ስለ ጨዋታው
“ጨዋታው በአጠቃላይ ጥሩ የሚባል ነበር፡፡በመጀመሪያው ዙር በሜዳውን ያሸነፈንን ይህን ቡድን ጥሩ ዝግጅት አድርገን ለማሸነፍ ችለናል፡፡”
ስለ ጠንካራ ጎናቸው
” በዛሬው ጨዋታ እንደከዚህ ቀደሙ ኳስ መስርተን መጫወት ችለናል ከዚህም በተጨማሪ በዛሬው ጨዋታ ረጃጅም ኳሶች እንዳይጣሉብን በጥንቃቄ መጫወት ችለናል፡፡”
ንጎሴ ደስታ – ወልዲያ
ስለ ጨዋታው
“ጨዋታው ከመነሻው ያለ አግባብ በተሰጠብን የፍፁም ቅጣት ምት የተነሳ በአእምሮ ረገድ ወርደው ነበር ከዚህም በተጨማሪ የመሀል ክፍላችን ኳስ በማደረጀትና የአጥቂ ክፍሉን በማገዙ ረገድ ጥሩ አልነበሩም፡፡”
ስለ ዳኝነት
“በጨዋታው ለመሸነፋችን አንዱ ምክንያት በመጀመሪያው ደቂቃዎች ያለ አግባብ የተሰጠብን ፍፁም ቅጣት ምት ነው፡፡በኢትዮጵያ የሚገኙት የዳኞች ስብእና እጅግ የሚያሳስብና የዳኝነት ስርአቱ እግርኳሱን የሚገድል አካሄድ ነው፡፡”