ዛሬ 10፡00 ላይ በተካሄደው የዝግጅት ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የዛምቢያ አቻውን አስተናግዶ 1-0 በሆነ ውጤት ተሸንፏል፡፡
በጨዋታው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣን ዮሃንስ ሳህሌ ዛምቢያን ሙሉ ለሙሉ በሃገር ውስጥ ተጨዋቾች የገጠሙ ሲሆን አምበል ሆኖ የተሾመው ስዩም ተስፋዬ ፣ ጀማል ጣሰው እና ሳላዲን በርጊቾ በጨዋታው ላይ አልተሳተፉም፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በዛሬው ጨዋታ የተጠቀመው ቡድን ይህንን ይመስላል፡-
አቤል ማሞ
ሞገስ ታደሰ ፣ አስቻለው ታመነ ፣ ሙጂብ ቃሲም ፣ ዘካርያስ ቱጂ
በኃይሉ አሰፋ ፣ ጋቶች ፓኖም ፣ ምንተስኖት አዳነ ፣ አስቻለው ግርማ
ቢንያም አሰፋ ፣ ባዬ ገዛኸኝ
የመጀመርያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ደከም ያለ እንቅስቃሴ ያሳየ ሲሆን የተጫዋቾች የመናበብ ችግርም ጎልቶ ታይቷል፡፡ በተለይም በአማካይ ክፍሉ ፈጠራ የማይታይበትና በማጥቃት እንቅስቃሴው እምብዛም የማይሳተፍ ሆኖ ታይቷል፡፡
ዛምቢያዎች የጨዋታውን ብቸኛ ግብ ከመረብ ያሳረፉት በ45ኛው ደቂቃ ሲሆን አማካዩ አለን ማኩካ በግንባሩ በመግጨት ከመረብ አሳርፏል፡፡ የመጀመርያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለጊዜም በመዳብ ጥይቶቹ 1-0 መሪነት ተጠናቋል፡፡
ከእረፍት መልስ አሰልጣን ዮሃንስ ጋቶች ፓኖምን በብሩክ ቃልቦሬ ፣ ምንተስኖትን በፍሬው ሰለሞን ከቀየሩ በኋላ የጨዋታው መልክ ተለውጧል፡፡ ዋልያዎቹ በተደጋጋሚ ወደ ግብ መድረስ ሲችሉ የኳስ ቁጥጥር የበላይነትም መውሰድ ችለዋል፡፡ በ60ኛው ደቂቃ ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጪ ፍሬው ሰለሞን የሞከራትን ኳስ ግብ ጠባቂው ዳኒ ሞንዮ በግሩም ሁኔታ ወደ ውጪ አውጥቷል፡፡
በ73ኛው ደቂቃ ግቧን ያስቆጠረው አለን ማኩካ በአስቻለው ግርማ ላይ በሰራው ያልተገባ አጨዋወት ኢትዮጵያ የፍፁም ቅጣት ምት ብታገኝም ቢንያም አሰፋ በግቡ አግዳሚ ወደ ውጪ ሰድዷታል፡፡
የጨዋታው ሁለት ሶስተኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ላይ ራምኬል ሎክ በበኃይሉ አሰፋ ፣ ኤፍሬም ቀሬ በባዬ ገዛኸኝ ተቀይረው ቢገቡም በጨዋታው ለውጥ መፍጠር አልቻሉም፡፡
ጨዋታው ሊገባደድ 5 ደቂቃዎች ሲቀሩ የብሄራዊ ቡድኑን ማልያ ለመጀመርያ ጊዜ ለብሶ የተጫወተው ሙጂብ ቃሲም ኳስን በእጅ በመንካቱ በሁለተኛ ቢጫ ከሜዳ ተሰናብቷል፡፡ ጨዋታውም በዛምቢያ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
በጨዋታው ዘካርያስ ቱጂ ፣ ሙጂብ ቃሲም እና ፍሬው ሰለሞን በኢትዮጵያ በኩል ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ አጥቂው ኢቫንስ ካንግዋ እና አማካዩ ናታን ሲንካላ ከዛምቢያ በኩል ድንቅ እንቅስቃሴ አሳይተዋል፡፡