የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ የአል-አህሊው ኮከብ ሳላዲን ሰኢድን የብሄራዊ ቡድኑ አምበል አድርገው መሾማቸውን ትላንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በይፋ ተናግረዋል፡፡
አሰልጣኙ ሳላዲንን ለአምበልነት የመረጡት ልምዱ ለመሪነት የሚያበቃው ስለሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ ሳላዲን በብሄራዊ ቡድኑ ከፍኛ ልምድ አካብቷል፡፡ የመምራት ልምዱ እንድመርጠው አድርጎኛል፡፡ በኃይሉ አሰፋ ደግሞ 2ኛ አምበል አድርገን መርጠነዋል፡፡ ›› ብለዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት ስዩም ተስፋዬ አምበል መደረጉ ከጭምጭምታ ያለፈ እንዳልሆነም አሰልጣኙ አብራርተዋል፡፡ ‹‹ የስዩም አምበልነት በጭምጭምታ ደረጃ የተወራ ነው፡፡ 44 ተጫዋቾች በመረጥንበት ሰአት ስዩም እና በኃይሉ ካሉት ውስጥ ልምድ ያላቸው ስለሆኑ እንዲያስተባብሩና ለተጫዋቾቹ ተጠሪ እንዲሆኑ ነበር የመረጥናቸው፡፡ ይህ ማለት ግን አምበል አድርገን መርጠናቸዋል ማለት አልነበረም፡፡ ምክንያቱም አሳማኝ አቋም ካላሳዩ ከሚቀነሱት ተጫዋቾች መካከል ሊሆኑ ይችሉ ነበር፡፡ ›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡