የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ባደረገው የመጀመርያ ጨዋታ የሌሴቶ ብሄራዊ ቡድንን 2-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡
ለመጀመርያ ጊዜ በባህርዳር በተደረገው በዚህ ጨዋታ ቁጥሩ ከ80-90 ሺህ የሚገመት ደጋፊ በስታድየም የተገኘ ሲሆን ከ7 ሰአት ጀምሮ ስታድየሙ በአስደናቂ ድበብ ደምቆ ውሏል፡፡
ዛሬ ሌሴቶን የገጠመው የብሄራዊ ቡድኑ ቋሚ አሰላለፍ ይህንን ይመስል ነበር (4-1-3-2) ፡-
አቤል ማሞ
ስዩም ተስፋዬ – ሳላዲን በርጊቾ – አስቻለው ታመነ – ዘካርያስ ቱጂ
ጋቶች ፓኖም
በኃይሉ አሰፋ – ሽመልስ በቀለ (ብሩክ ቃልቦሬ) – ኡመድ ኡኩሪ (ራምኬ ሎክ)
ሳላዲን ሰኢድ – ጌታነህ ከበደ (ባዬ ገዛኸኝ)
በጨዋታው የመጀመርያ አጋማሽ የሌሴቶ ብሄራዊ ቡድን በእንቅስቃሴ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተሸሎ የተገኘ ሲሆን ወደ ግብ በመድረስ በኩልም ከኢትዮጵያ ተሸለው ተገኝተዋል፡፡ አስደናቂውን የስታድየም ድባብ ወደ ፀጥታ የቀየሩትም በመጀመርያው አጋማሽ ባስቆጠሩት ግብ ታግዘው ነው፡፡ የመጀመርያው አጋማሽ በሌሴቶ ብሄራዊ ቡድን 1-0 መሪነት ሲጠናቀቅ ዋልያዎቹ ተስፋ የሚሰጥ እንቅስቃሴ ማሳየት ተስኗቸው ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ዋልያዎቹ ግብ ለማስቆጠር ጫና ፈጥረው የተንቀሳቀሱ ሲሆን ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ በስታድየሙ በጣለው ድንገተኛ ከባድ ዝናብም የሌሴቶ ብሄራዊ ቡድን ላይ ጫና ፈጥሮባቸው ታይቷል፡፡
የቡናው አማካይ ጋቶች ፓኖም ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውጪ አክርሮ የመታት ኳስ በግሩም ሁኔታ ከመረብ አርፋ ኢትዮጵያን አቻ አድርጋለች፡፡ ከግቡ በኋላ የበለጠ ጫና ፈጥረው የተንቀሳቀሱት ዋልያዎቹ በጌታነህ ተቀይሮ በገባው ባዬ ገዛኸኝ እና በኡመድ ኡኩሪ የተተካው ራምኬል ሎክ ታግዘው የማጥቃት ጫናቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ የአል አህሊው አጥቂ ሳላዲን ሰኢድም የሌሴቶ ተከላካዮች የፈጠሩት ስህተትን ተጠቅሞ ኢትዮጵያን 2-1 እንድትመራ ያስቻለች ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ጨዋታውም በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡
በጨዋታው ዋልያዎቹ ግቦችን ባስቆጠሩባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት ደጋፊዎች ወደ ሜዳ ገብተው ደስታቸውን የገለፁበት እና ውድ የመግቢያ ዋጋ የተጠየቀበት የስታድየሙ ክፍል በሰፋፊ የካፍቴርያ ጥላዎች መሸፈን የእለቱ አነጋጋሪ ክስተቶች ሆነው አልፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የዛሬ ድሉ ከ2 አመታት በኋላ የተገኘ የመጀመርያ የሜዳ ድሉ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ቡድኑ በጁላይ 2014 ሩዋንዳን በቻን ማጣርያ አዲስ አበባ ላይ በአስራት መገርሳ ግብ 1-0 ካሸነፈ ወዲህ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ፣ በአለም ዋንጫ ማጣርያ እና የወዳጅነት ጨዋታዎች ጭምር ድል አስመዝግቦ አያውቅም፡፡
ኢትዮጵያ ዛሬ ያሳካችውን ድል ተከትሎ ትላንት ሲሸልስን 4-0 ያሸነፈችው አልጄርያን ተከትላ በምድቧ 2ኛ ደረጃን ይዛለች፡፡