አሰልጣን ዮሃንስ ሳህሌ ነገ ብሄራዊ ቡድናችን ከኬንያ አቻው ጋር ከሚያደርገው የቻን ማጣርያ ጨዋታ በፊት ዛሬ ምሽት በግራንድ ሪዞርት መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ አሰልጣኙ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ካነሷቸው ሃሳቦች ዋና ዋናዎቹን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
ስለ ዝግጅታቸው
‹‹ እስካሁን ዝግጅታችንን በጥሩ ሁኔታ እያደረግን ነው፡፡ የምናደርጋቸውን ልምምዶች ቪድዮ እየተመለከትን እንገመግማለን፡፡ ልምምዶቹን የምንመለከተው ለትችት ሳይሆን ለመገምገም እና ከስህተቶቻችን ለመማማር ነው፡፡ ህዝባችንን በድጋሚለ ማስደሰት ተጫዋቾቹ እና የአሰልጣኝ ቡድኑ ዝግጁዎች ነን፡፡››
ስለ ኬንያ
‹‹ ስለ ኬንያ የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ሃገር በቀል ተጫዋች ስለሆኑ እነሱ ላይ ምንም መረጃ የለንም፡፡ ››
ቻን
‹‹ ቻን ከሌሎች ውድድሮች የተለየነው፡፡ አላማውም የተለየነው፡፡ ሌሎች ውድድሮች የተጫዋች ገደብ የላቸውም፡፡ በዚህኛው ደግሞ የኢንተርናሽናል ጨዋታ ልምድ የሌላቸው እና ሃገር በቀል ተጨዋቾች ይሳተፋሉ፡፡ ይህ ውድድር ከታላላቆቹ የአፍሪካ ሃገራት በተለየ እኛን ይጠቅመናል፡፡ ምክንያቱም በሌሶቶው ጨዋታ ከተጠቀምናቸው ተጫዋቾች መካከል 4 ተጫዋቾችን ብቻ ነው መጠቀም የማንችለው፡፡ ››
‹‹ ውጤት እንዳለ ሆኖ የውድድሩ አላማ የተጫዋቾችን ደረጃ ማሳደግ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ተጫዋቾች ቻን ባይኖር ኖሮ የመታየት እድል አያገኙም ነበር፡፡ ለኛ ቻን ከምንም በላይ የሚጠቅመን የኢትዮጵያ እግርኳስ ደረጃ የት ላይ እንዳለ የምናይበት በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ውድድር ባይኖር ሁልጊዜም የምናስበው ስለ ዋናው ብሄራዊ ቡድን ብቻ ይሆን ነበር፡፡ ተተኪውን ማዘጋጀት ላይ እንዳናተኩር ያደርገን ነበር፡፡ ስለዚህ ቻን የሚሰጠንን አድቫንቴጅ በሚገባ እጠቀምበታለን፡፡ ››
የቡድን ውህደት
‹‹ (ከዛምቢያ ጋር በተደረገው ጨዋታ) አንድ እና ሁለት ቀን ብቻ ተለማምዶ ጨዋታ ያደረገ ቡድን ጨዋታው ቢከብደው ፣ ተጫዋቾቹ ቢደናበሩ ፣ ራሳቸው ላይ ግብ ቢያስቆጥሩ አይገርመኝም ነበር፡፡ በዛምቢያው ጨዋታ አለመቀናጀታችን የሚደንቅ አልነበረም፡፡ በዛ ላይ 6 ተጫዋቾች (በሌሶቶ ጨዋታ ላይ የተጫወቱ) አልተሰለፉም ነበር፡፡ ከዛ ጨዋታ በኋላ 13 ቀናት ልምምድ ሰርተናል፡፡ ስህተታችንን የማረም እድልም አግኝተናል፡፡ ስለዚህ አሁን ካለጥርጥር ከዛምቢያው ጨዋታ የተሻለ ነገር ይዘን እንቀርባለን፡፡››
የህዝብ ጫና
‹‹ 100 ሺህ ህዝብ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ደረጃ ታይቶ የማይታወቅ ነው፡፡ በዚህ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ታጅቦ መጫወት ይከብዳል፡፡ ግብ ጠባቂው እና ሁለቱ ተከላካዮች ለመጀመርያ ጊዜ በነጥብ ጨዋታ የተሰለፉበት ነበር፡፡ ከነሱ በተጨማሪም ሁሉም ተጫዋች በ100 ሺህ ደጋፊ ፊት ተጫውቶ አያውቅም፡፡ ስለዚህ በመጀመርያው አጋማሽ በራስ መተማመናችን ቢወርድ አይገርምም ነበር፡፡ ››
‹‹ የመጀመርያው አጋማሽ ቢፈትነንም በሁለተኛው ግማሽ የሕዝቡን ጫና መቋቋምና እንደውም እንደ መነሳሻ በመውሰድ ውጤት ይዘን መውጣት ችለናል፡፡ ከመመራት ተነስተን አሸንፈን መውጣታችን በራሱ በራስ መተማመናችንን ያሳያል ብዬ አስባለሁ፡፡ ››