‹‹ በጨዋታው የተሻልን ስለነበርን አሸንፈናል ›› ዮሃንስ ሳህሌ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የኬንያ አቻውን 2-0 ካሸነፈበት ጨዋታ በኋላ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡ አሰልጣኙ ከሰጡት አስተያየት ዋና ዋናዎቹን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል፡፡

 

ስለ ጨዋታው

‹‹ በጨዋታው የተሻልን ስለነበርን አሸንፈናል፡፡ እነርሱ ከፍ ፁም ቅጣት ምቱ ውጪ እምብዛም የግብ እድል መፍጠር አልቻሉም፡፡ እኛ ደግሞ የተሻለ ወደ ግብ ለመቅረብ ሞክረናል፡፡ በአካል ብቃቱም የተሻልን ነበርን፡፡ ግዙፎች ቢሆኑም በፍጥነት እና ጫና በመፍጠር በልጠናቸዋል፡፡ ከዚህ በፊት የታማንባቸው ነገሮችን አሻሽለን ቅበናል፡፡ ክፍተት አለ ፣ ቅንጅት የለም ለሚሉ በአጭር ጊዜ መልስ የሚሰጥ አቋም አሳይተናል፡፡ ››

 

የምንተስኖት አዳነ ቅያሪ

‹‹ የምንተስኖት አዳነ ቅያሪ ታክቲካዊ ነበር፡፡ በጨዋታው መጀመርያ መሃል ሜዳው ክፍት ነበር፡፡ ተቀይሮ የገባው ፍሬው ሰለሞን መከላከሉ ላይ ጥሩ ነበር፡፡ ልምድ የሌለው በመሆኑ ኳስ ሲበላሽበት እና ሲደነግጥ ነበር፡፡ ነገር ግን ከሱ የምጠብቀውን እንቅስቃሴ አድርጓል፡፡ ››

 

አዳዲስ ፊቶች

‹‹ በጨዋታው አዲስ ፊት የነበሩት አስቻለው ግርማ እና ተካልኝ ደጀኔ ከጠበቅነው በላይ አቋም አሳይተዋል፡፡ ለዚህ ተጠቃሹ ደግሞ ደጋፊው ነበር፡፡ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የሰጡን ድጋፍ ለተጫዋቾቹ ትልቅ መነሳሳትን ፈጥሮላቸዋል፡፡ ››

 

የፍፁም ቅጣት ምት

‹‹ የፍፁም ቅጣት ምቱን መሳታቸው እኛን የበለጠ ሲያነሳሳን እነርሱን ደግሞ ሞራላቸውን ዝቅ አድርጎታል፡፡ በሃገራችን ፍፁም ቅጣት ምት ማዳን ልተለመደ በመሆኑም የግብ ጠባቂዎቻችንን ሞራል ያነሳሳል፡፡ ››

 

የመልሱ ጨዋታ

‹‹ የመልሱ ጨዋታ አዲስ ነው፡፡ 0-0 ነው የምንጀምረው፡፡ እኛ እዚህ አሸንፈናቸዋል፡፡ እነርሱም በሜዳቸው ሊያሸንፉን ይችላሉ፡፡ ስለዚህ የዛሬው ድል አያዘናጋንም፡፡ ››