ለሴት ሰልጣኞች ብቻ ሲሰጥ የቆየው የካፍ የአሰልጣኞች ስልጠና ተጠናቀቀ

በኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና በካፍ አማካኝነት ከሰኔ 21 እስከ ሐምሌ 5 ቀን ድረስ ሲሰጥ የቆየው የ C ላይሰንስ ዛሬ ረፋድ ላይ የኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደት አቶ ጁነዲን ባሻ እና የስራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት  ዶ/ር ነስረዲን በክብር እንግድነት በተገኙበት አምቦ በሚገኘው የፊፋ ጎል ፕሮጀክት ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡

36 ሴት ሰልጣኞች የተሳተፉበት ይህ ስልጠና በኢትዮጵያም ሆነ በምስራቅ አፍሪካ ለሴቶች ብቻ የተሰጠ ቀዳሚው ስልጠና ሲሆን አምስቱም ስልጠናውን የሰጡት ኢትዮዽያውን የካፍ ኢንስትራክተሮች መሆናቸው ልየዩ ያደርገዋል ተብሏል፡፡

ለ15 ቀን በቆየው በዚህ ስልጠና በአጠቃላይ የ C  ላይሰንስ ማንዋል ሊያሟላ የሚገባቸው ነገሮች በሙሉ የስልጠናው አካል እንደነበር የተገለፀ ሲሆን የጨዋታ ህጎችም የስልጠናው አካል ነበሩ፡፡ ስልጠናውም በቃል እና በተግባር ላይ ያተኮረ እውቀት እንዲያገኙ መደረጉን ለማወቅ ችለናል። በስልጠናውም ወቅት ሰልጣኞቹ የነበራቸው የማወቅ ፍላጎት እና ያሳዮት ተነሳሽነት ወደፊት በርካታ ሴት ሰልጣኞች በዘርፉ ሊገኙ እንደሚችል ጠቁሞ ያለፈ ስልጠና ነበር ተብሏል።


በአጠቃላይ በተግባርም ሆነ በቃል የወሰዱት ትምህርት እና ያስመዘገቡት ውጤት ኢንስትራክተሮቹ ለካፍ በቅርቡ አሳውቀው የ C ላይሰንሱ ማረጋገጫ ሰርተፍኬት እንደሚሰጥ ለማወቅ ችለናል ።

በሴቶች እግር ኳስ አቋሟቸው ሳይዋዥቅ ለረጅም ጊዜ ከተጫወቱ ተጫዋቾች መካከል አንዷ የሆነችው የኢትዮዽያ ንግድ ባንኳ ብዙሀን እንዳለ ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል አንዷ የነበረች ሲሆን በቆይታዋ ጠቃሚ እውቀት እንዳገኘችና ወደፊትም ተጨማሪ ስልጠናዎችን ለማግኘት እንዳሰበች ገልጻለች፡፡ ስልጠናውን መውሰዷን ተከትሎም የእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመኗ ሊያበቃ ይችላል ወይ ተብላ ለተጠየቀችው ጥያቄ በቅርቡ ጫማ የመስቀል ሀሳብ እንደሌላት ተናግራለች ።

ሌላዋ የአዳማ ከተማ አንጋፋ አጥቂ እንደገና አለምዋሶ በ1990ዎቸቹ ከነበራት ስኬታማ የእግርኳስ ህይወት በኋላ ወደ ህክምና ትምህርቷ በማተኮር በህክምና ዶክትሬት ዲግሪዋን የያዘች ሲሆን አሁን ካለፈው አመት ጀምሮ ወደ ተጫዋቾነት ተመልሳ ለአዳማ እየተጫወተች ትገኛለች፡፡ አሁን ደግሞ በአምቦ በተሰጠው የአሰልጣኝነት ስልጠና ላይ ተካፍላለች፡፡ በስልጠናው ጥሩ ጊዜ እንዳሳለፈችም ተናግራለች፡፡

በኢትዮጵያ ሴቶች እግርኳሰ ላይ የሴት አሰልጣኞች ቁጥር እጅግ ዝቅተኛ ሲሆን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ጥረት እና ኢትዮጵያ ቡና ውጪ ሌሎች የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ክለቦች የሚመሩት በወንድ አሰልጣኞች መሆኑ እንደዚህ አይነት ስልጠናዎች ተጨማሪ ሴት አሰልጣኞችን ወደ እግርኳሱ ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *