የክለቦች የዝውውር እንቅስቃሴ | ድሬዳዋ ከተማ

የኢትዮጵያ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ዛሬ በይፋ የተከፈተ ሲሆን ድሬዳዋ ከተማም በርካታ ተጫዋቾችን ለማስፈረም ከስምምነት ላይ በመድረስ ቀዳሚው ክለብ ሆኗል፡፡ ክለቡ ዘንድሮ ያሳለፈውን መጥፎ የውድድር ዘመን በቀጣዩ አመት አሻሽሎ ለመቅረብ በስብስቡ ላይ ጉልህ ለውጥ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ለመፈረም የተስማሙ ተጫዋቾች

ብሩክ ቃልቦሬ እና ሞገስ ታደሰ

ያለፉትን ሁለት የውድድር ዘመናት በአዳማ ከተማ ያሳለፈው ብሩክ ቃልቦሬ ለድሬዳዋ ከተማ ለመፈረም የተስማማ ተጫዋች ነው፡፡ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ወደ ጅቡቲ የሚጓዘው ብሩክ ከጉዞ መልስ ይፈርማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በአዳማ ከተማ ዘንድሮ እምብዛም ግልጋሎት ማበርከት ያልቻለው ሞገስ ወደ ድሬዳዋ በማምራት በርካታ ተከላካዮችን የሰበሰበውን ቡድን ለመቀላቀል ተስማምቷል፡፡

ከሲዳማ ቡና…

አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ከቀድሞ ክለባቸው ሲዳማ ቡና በርካታ ተጫዋቾች አስኮብልለዋል፡፡ ከአርባምንጭ ሲዳማን ከተቀላቀለ በኋላ ድንቅ ሁለት አመታትን ያሳለፈው አንተነህ ተስፋዬ በከፍተኛ ገንዘብ ወደ ሞቃታማዋ ከተማ ሲያመራ አንጋፋው አጥቂ ኤሪክ ሙራንዳ ከ3 የውድድር ዘመን የሲዳማ ቡና ቆይታ በኋላ የእግርኳስ ህይወቱን በድሬዳዋ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ሌላው ኬንያዊ ሰንደይ ሙቱኩ ከድንቅ አንድ የውድድር አመት የሲዳማ ቆይታ በኋላ ወደ ድሬዳዋ ሲያመራ ሔይቲያዊው ሁለገብ ሳውሬል ኦልሪሽም የቡድን አጋሮቹን ተከትሎ ወደ ድሬዳዋ ለማቅናት የተስማማ ተጫዋች ነው፡፡ የግራ መስመር ተከላካዩ ወሰኑ ማዜ ወደ ዘላለም ሽፈራው ስብስብ እንደተቀላቀለ የተነገረለት ሌላው የሲዳማ ቡና ተጫዋች ነው፡፡

ዘካርያስ ፍቅሬ

የከፍተኛ ሊጉ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ዘካርያስ ፍቅሬ ወደ ድሬዳዋ ለማቅናት መስማማቱ ተነግሯል፡፡ አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ባለፈው ሰኞ ሀዲያ ሆሳዕና ከ ሀላባ ከተማ ያደረጉትን ጨዋታ በስፍራው ተገኝተው መመልከታቸውም የተጫዋቹ ማረፊያ ይበልጥ ወደ ድሬዳዋ እንዲያጋድል አድርጎታል፡፡

አህመድ ረሺድ

ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የተለያየው አህመድ ከቡድኑ ከፍተኛ ተከፋዮች አንዱ ሆኖ ወደ ድሬዳዋ ከተማ ያመራ ሲሆን በማጥቃት ረገድ ደካማ በሆነው የድሬዳዋ ከተማ የመስመር ተከላካይ ስፍራ ላይ ለውጥ ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በድርድር ላይ ያሉ

ከቅዱስ ጊዮርጊስ እንደሚለቁ ከሚጠበቁ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ዘካርያስ ቱጂ ብርቱካናማዎቹን ለመቀላቀል ድርድር ላይ እንደሚገኝ የታወቀ ሲሆን ከኤሌክትሪክ ጋር ውሉን የጨረሰው ብሩክ አየለ ከቀድሞ አሰልጣኙ ጋር ሊገናኝ ይችለል ተብሏል፡፡ የሀዲያ ሆሳዕናው ኄኖክ አርፊጮም በክለቡ ከሚፈለጉ ተጫዋቾች መካከል ነው፡፡

ውላቸውን ያደሱ

አምበሉ ሳምሶን አሰፋ በክለቡ  ለተጨማሪ ሁለት አመታት ለመቆየት የተስማማ ሲሆን ሌሎች ኮንትራታቸው የተጠናቀቁ ተጫዋቾች በክለቡ ኮንትራት ላይቀርብላቸው እንደሚችልና የመውጫው በር ላይ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡

የለቀቁ/የሚለቁ ተጫዋቾች

በ6 ወራት ኮንትራት ክለቡን ተቀላቅሎ የነበረው አምሀ በለጠ ወደ ሲዳማ ቡና ያመራ ሲሆን በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ክለቡን የሚለቁ ከ10 የማያንሱ ተጫዋቾች ይፋ እንደሚሆኑ ታውቋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *