የኢትዮዽያ አንደኛ ሊግ የማጠቃልያ ውድድር በድሬደዋ ከተማ አስተናጋጅነት ከሐምሌ 8 እስከ 16 በየምድባቸው ወደ ከፍተኛ ሊጉ ማለፋቸውን አስቀድመው ባረጋገጡ ስድስት ቡድኖች መካከል ይደረጋል፡፡
ዛሬ 09:00 ላይ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ትንሿ አዳራሽ የዕለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት የድሬዳዋ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሀር ፣ የኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሊግ ኮሚቴ የስፖርት ማዘውተርያ ዋና ዳሬክተር አቶ ሰለሞን ገ/ስላሴ እና የክለብ ተወካይ አመራሮች በተገኙበት የእጣ ማውጣት ስነ ስርአት ተካሂዷል፡፡ የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ ከድር ጁሀር የፍቅር እና የመቻቻል ተመስሌት ወደ ሆነችው ድሬደዋ እንኳን ደና መጣችሁ በማለት ተሳታፊዎች በድሬዳዋ በሚኖራቸሁ ቆይታ አስደሳች እና የተሳካ ውድድር እንዲያሳልፉ መልካም ምኞታቸውን በመግለፅ የመርሐግብሩን መጀመር አብስረዋል።
በመቀጠል አቶ ሰለሞን በውድድሩ ላይ የተለየ ህገ ደንብ እንደሌለ ገልፀው አመቱን ሙሉ ሲካሄድበት የነበረው የውድድር ደንብ በዚህ ማጠቃልያ ውድድር እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ በመጨረሻም ይህ የማጠቃልያ ውድድር የውድድሩን ቻምፒዮን ለመለየት ተብሎ የተዘጋጀ መሆኑን ገልፀው ከተሳታፊዎቹ የተወሰኑ የማብራርያ ጥያቄዎች ቀርበው ምላሽ ከተሰጠበት በኋላ ቀጥታ ወደ ዕጣ ማውጣት ስነ ስርአት አምርተዋል።
የዕጣ ድልድሉ ይህንን ይመስላል፡-
ምድብ ሀ
የካ ክ/ከተማ
ቡታጅራ ከተማ
መቂ ከተማ
ምድብ ለ
አምበሪቾ
ሚዛን አማን
ደሴ ከተማ
የመጀመርያ ቀን መርሐግብር
ቅዳሜ ሐምሌ 8
08:00 የካ ከ ቡታጅራ ከተማ
10:00 አምበሪቾ ከ ሚዛን አማን
መቂ ከተማ እና ደሴ ከተማ አራፊዎች ይሆናሉ
ከየምድባቸው አንደኛ እና ሁለተኛ የሚወጡ ቡድኖች በቀጥታ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ሲያልፉ የምድብ ሀ አንደኛ ከምድብ ለ ሁለተኛ የምድብ ለ አንደኛ ከምድብ ሀ ሁለተኛ ጋር በግማሽ ፍፃሜው ይጫወቱና አሸናፊዎቹ እሁድ ሐምሌ 16 ቀን ለዋንጫ ተጫውተው የውድድሩ ፍፃሜ ይሆናል።