አንደኛ ሊግ | ደሴ ከተማ እና የካ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅለዋል

የኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር የምድብ ጨዋታዎች ዛሬ ረፋድ ሲጠናቀቁ ደሴ ከተማ እና የካ ክፍለ ከተማ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ማለፋቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ጠዋት 02:00 ላይ በተካሄደው የምድብ ሀ የመጨረሻ ጨዋታ ቡታጅራ ከተማ ከ ከመቂ ከተማ ተገናኝተው መቂ ከተማ 4-2 በሆነ ውጤት በማሸነፍ በቀዳሚነት ወደ ግማሽ ፍጻሜው ተሸጋግሯል፡፡

ቀዝቀዝ ብሎ በጀመረው በሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ጎል በማስቆጠር ቀዳሚ የነበረው መቂ ነበር፡፡ በአንድ ሁለት ቅብብል በግሩም ሁኔታ ቦንሳ ኑራ አስቆጥሯል፡፡ የቡታጅራው ተከላካይ የግብ ክልል ውስጥ ያለ ኳስ ሆን ብሎ በእጅ ነክቶ በማስቀረቱ ቹቹ ሻውል ቀይ ካርድ ተመልክቶ ከሜዳ ሲወጣ ለመቂ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ተመስገን ሽብሩ ወደ ጎልነት በመቀየር የመቂን መሪነት ወደ ሁለት አስፍቶ ወደ እረፍት አምርተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ በጎዶሎ ተጫዋቾች የተጫወቱት ቡታጅራዎች በአቤል ሽጉጤ እና ክንዴ አቡቸ አማካኝነት ጎሎችን አስቆጥረው አቻ መሆን ቻሉ። አቻ መውጣት ወደ ግማሽ ፍጻሜው ያሳልፋቸው የነበረው ቡታጅራዎች ጨዋታውን በመቆጣጠር እየተንቀሳቀሱ ባሉበት ሁኔታ የመቂው በላይ ታደሰ የጎል መስመሩን ሳያልፍ በርቀት የነበሩት ረዳት ዳኛ ጎል ነው በማለታቸው ዋናው ዳኛ አፅድቀውት ለመቂ ሦስተኛ ጎል ተቆጠረ። በዚህ ውሳኔ ቅር የተሰኙት ቡታጅራዎች የክስ ሪዘርቭ አይዘው ጨዋታው ቀጥሏል።

ቡታጅራዎች ይህን ውጤት አስጠብቀው ጨዋታውን ቢያጠናቅቁ ወደ ግማሽ ፍፃሜ የሚያሳልፋቸው ቢሆንም በጨዋታው መጠናቀቂያ የመጨረሻ ደቂቃ ላይ ቦንሳ ኑራ ለራሱ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በመቂ 4-2 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ መቂ ከተማ በ6 ነጥቦች በአንደኝነት ወደ ግማሽ ፍጻሜ ሲያልፍ ቡታጅራ በ2 ጎል ልዩነት መሸነፉን ተከትሎ የካ በ1 ነጥብ ብቻ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ተቀላቅሏል፡፡

04:00 ላይ ሚዛን አማንን ከ ደሴ ከተማ ያገናኘውን ጨዋታ ደሴ ከተማ 3-1 በማሸነፍ ደሴ ከተማ ሀንበሪቾን በመከተል የግማሽ ፍፃሜው አላፊ ቡድን ሆኗል፡፡
ጠንካራ ፉክክር በተስተናገደበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ቀድሞ ጎል በማስቆጠር በጨዋታው ብልጫ የነበራቸው ሚዛን አማኖች ሲሆኑ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ዘላለም መላኩ ነበር ጎሉን ያስቆጠረው። የመጀመርያው አጋማሽም ተጨማሪ ጎል ሳይስተናገዱ በሚዛን አማን 1-0 መሪነት ተጠናቋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ደሴ ከተማዎች ሙሉ ለሙሉ ተጭነው የተጫወቱ ሲሆን የሚዛን አማኑ ተጫዋች ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ኳስ በእጅ በመንካቱ ቀይ ካርድ ተመልክቶ በተሰጠ የፍፁም ቅጣት ምት እዮብ ካህሳይ ወደ ጎልነት ቀይሮ ደሴን አቻ አድርጓል።

ደሴ ከተማዎች በጎሉ መቆጠር ተነቃቅተው ተጭነው ሲጫወቱ በጣም ግልፅ የሆኑ እና ለማመን የሚከብዱ ኳሶችን በአብደላ እሸቱ እና ተስፋ ወሰን አማካኝነት አምክነዋል፡፡

ደሴዎች ጫና መፍጠራቸውን ቀጥለው በእሱባለው አንለይ ጎል አማካኝነት መሪ መሆን ሲችሉ አቻ መውጣት ወደ ግማሽ ፍጻሜው የሚያሳልፋቸው ሚዛኖች ግብ ለማስቆጠር እያጠቁ ባለበት ሰአት ለደሴ ከነማ ማሸነፍ ትልቅ ሚና የነበረው እዮብ ካህሳይ ለራሱ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ ደሴን ወደ ግማሽ ፍፃሜ መርቶታል፡፡ ጨዋታውም በደሴ ከተማ 3 – 1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ ከምድብ ለ ሀምበሪቾ በ4 ነጥቅ አንደኛ ፣ ደሴ ከተማ በ3 ነጥብ ሁለተኛ በመሆን ወደ ግማሽ ፍፃሜው አላፊ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታው አርብ ሲካሄድ 08:00 ላይ መቂ ከተማ ከ ደሴ ከተማ ፤ 10:00 ሀምበሪቾ ከ የካ ክፍለከተማ ጋር የሚጫወቱ ይሆናል፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *