አነጋጋሪ ሀሳቦች የተነሱበት የካፍ ሲምፖዝየም …

በሞሮኮ ርዕሰ መዲና ራባት ለሁለት ቀናት ስለ አህጉሪቱዋ የእግር ኳስ እድገት ከየሀገራቱ ከተወጣጡ የእግር ኳስ ሬደሬሽን አመራሮች፣ የቀድሞ ተጨዋቾች እንዲሁም ጥሪ ከተደረገላቸው እንግዶች ጋር በመሆን ምክክር ሲደረግበት የነበረው የካፍ ሲምፖዝየም ተጠናቋል፡፡

በሲምፖዚየሙ ስለ አፍሪካ ዋንጫ ውድድር፣ አፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት የሚጠይቁ ሀገራት ማሟላት ስላለባቸው ጉዳዮች፣ ስለ ክለብ ውድድሮች፣ ስለ ወጣቶች እግር ኳስ፣ ስለ አጠቃላይ የአህጉሪቱዋ እግር ኳስ እድገት፣ ስለ መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም ስለ ቴሌቪዥን መብት እና ተያያዥ ጉዳዮች ምክክር ሲደረግ የአብዛኛውን የተሳታፊ ትኩረት የገዛው ግን አፍሪካ ዋንጫ የሚካሄድበት ወቅትን መቀየር እና የተሳታፊ ሀገራትን ከ16 ወደ 24 ይደረግ ተብሎ የተነሳው ሀሳብ ነበር፡፡

ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያውያን የጊዜ አቆጣጠር ጥር ላይ ሲደረግ የነበረውን የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ወደ ሰኔ የመውሰድ አላማ እንዳለቸው በሲምፖዚየሙ የመክፈቻ ቀን የተናገሩት የካፍ ፕሬዝደንት አህመድ አህመድ እንደ ምክንያት ያቀረቡት በአውሮፓ እና በሌሎች አህጉራት የሚጫወቱ አፍሪካውያን ተጨዋቾች ከሚጫወቱበት የክለብ ውድድር አቋርጠው እንዳይመጡ፣ ሁለቱም ወገኖች በዚህ ውድድር ምክንያት እንዳይጎዱ በማሰብ እና ውድድሩ የሚገኘውን የቴሌቭዥን መብት ሽያጭ ገቢ እና ስፓንሰሮችን ከመሳብ አንፃር ከግምት ውስጥ ከማስገባት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ከአህመድ በፊት የአፍሪካን እግር ኳስ ለ29 አመታት የመሩት ኢሳ አያቱ ውድድሩ ወደ ሰኔ እንዳይሄድ እንደ ዋነኛ ምክንያትነት ለእግርኳስ ጨዋታ ያልተመቸው የአየር ሁኔታውን አንስተው ሲከራከሩ መቆየታቸው የሚታወስ ቢሆንም አህመድ ግን ለውጥ መምጣት እንዳለበት አምነዋል፡፡

የአፍሪካ ዋንጫ ውድድርን ላይ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ እና የኮንፌደሬሽን ዋንጫ የውደድር ጊዜያትም ላይ ለውጥ የማድረግ አላማ ያላቸው የ57 አመቱ አህመድ ከዚህ ቀደም በነበረው አደረጃጀት ወደፊት መጓዝ እንደማይችሉ እና ለውጦች መደረግ እንደሚጀምሩ ተናግረዋል፡፡

ከአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ ሃገራት ቁጥር መጨመር ጋር በተያያዘ ከ24 ሃገራት 20 ወይም 21 የአፍሪካ ሃገራት ሲሆኑ 3 ወይም 4 የሚሆኑ ከአፍሪካ አህጉር ውጪ የሚገኙ ተጋባዥ ሃገራት እንዲሆኑ በሲምፓዚየሙ ተነስቷል። የአፍሪካ ዋንጫን ከአህጉሪቱ ውጪ ባሉ ሃገራት ማስተናገድ የሚሉ ሃሳቦችም ሲንሸራሸሩ ነበር።

በአፍሪካ ዋንጫ ላይ የተሳታፊ ሀገራትን ቁጥር ከ16 ወደ 24 ካደገ አቅማቸው በእግር ኳሱ ብዙም ያልፈረጠሙ ሀገሮችን በውድድሩ ላይ እንዲሳተፉ ተጨማሪ እድሎችን ከመክፈቱ በላይ ብዙ ጨዋታዎች ባሉ ቁጥር የሚመጡ የቴሌቪዥን እና የስታዲየም ገቢ እንዲሁም ተያያዥ ገቢዎችን ለማግኘት እንደሚጠቅማቸው በማንሳት ነበር፡፡ የካፍ ስራ አስፈፃሚ እና ጠቅላላ ጉባኤ የተነሱ የመፍትሄ ሃሳቦች ላይ አርብ ውሳኔ እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *