ኄኖክ አዱኛ እና ይሁን እንደሻው ወደ ጅማ ከተማ አምርተዋል

የከፍተኛ ሊጉን በቀዳሚነት አጠናቆ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያደገው ጅማ ከተማ የቀኝ መስመር ተከላካዩ ኄኖክ አዱኛ እና አማካዩ ይሁን እንደሻውን የግሉ አድርጓል፡፡

ኄኖክ ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት በድሬዳዋ ከተማ መልካም ጊዜያት ማሳለፍ የቻለ ሲሆን ኮንትራቱ መጠናቀቁን ተከትሎ ስሙ ከኤሌክትሪክ እና አዳማ ከተማ ጋር በስፋት ሲያያዝ ቆይቶ በመጨረሻ ለጅማ ፈርሟል፡፡ የተዋጣለት የማጥቃት እንቅስቃሴ ከሚያደርጉ ጥቂት የመስመር ተከላካዮች አንዱ የሆነው የቀድሞ የሀላባ ከተማ ተከላካይ ኄኖክ ጅማን በሁለት አመት ኮንትራት ነው የተቀላቀለው፡፡

ይሁን እንደሻው ሌላው ጅማ ከተማን የተቀላቀለ ተጫዋች ነው፡፡ ከድሬዳዋ ጋር የነበረው ውል መጠናቀቁን ተከትሎ በውል ማራዘምያ ላይ ከክለቡ ጋር መስማማት ያልቻለው ይሁን የቡድን ጓደኛው ኄኖክን ተከትሎ ወደ ጅማ አምርቷል፡፡

ይሁን በ2007 ድሬዳዋን ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲያድግ ትልቁን ሚና ከተጫወቱ ተጫዋቾች መካከል የነበረ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሊግ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ መመረጡም የሚታወስ ነው፡፡

ጅማ ከተማ በዝውውር መስኮቱ የፕሪምየር ሊግ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችን በማስፈረም ላይ የሚገኝ ሲሆን ባለፈው ሳምንት አሸናፊ ሽብሩ እና ቢንያም ሲራጅን ማስፈረሙ ይታወሳል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *