በኢትዮጵያ ዋንጫ ሩብ ፍፃሜ የአምናው የፍፃሜ ተፋላሚ ቅዱስ ጊዮርጊስ አርባንጭ ከነማን አሸነፎ ግማሽ ፍፃሜውን ሲቀላቀል መከላከያ ሲዳማን በቀላሉ አሸንፎ ግማሽ ፍፀሜውን የተቀላቀለ ሁለተኛው ቡድን ሆኗል፡፡
በ9፡00 አርባምንጭ ከነማን የገጠመው ቅዱ ጊዮርጊስ 1-0 አሸንፏል፡፡ ፈረሰኞቹ በጨዋታው ሙሉ የጠጨዋ ብልጫ የነበራቸው ሲሆን በርካታ የግብ ሙከራዎችን ማድረገግ ችለዋል፡፡ በአንፃሩ አርባምንጭ ከነማዎች ወደ መለያ ፍፁም ቅጣት ምት ማምራትን የመረጡበት የሚመስል የመከላከል አጨዋወትን ለመተግበር ሞክረዋል፡፡
በጨዋታው ፈረሰኞቹ በምንተስኖት አዳነ ፣ ፍፁም ገ/ማርያም ፣ አዳነ ግርማ እና ተቀይሮ ገብቶ መልካም እቅስቃሴ ባሳየው አቡበከር ሳኒ አማካኝነት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ቢያደርጉም የማሸነፍያዋን ግብ ለማግኘት እስከ 86ኛው ደቂቃ መጠበቅ አስፈልጓቸዋል፡፡
ወጣቱ አማካይ ናትናኤል ዘለቀ በግምት ከ25 ሜትር ርቀት በግሩም ሁኔታ ከመረብ ያሳረፋት ግብ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ1-0 አሸናፊነት ግማሽ ፍፃሜውን እንዲቀላቀል አስችላዋለች፡፡
በ11፡30 የተገናኙት መከላከያ እና ሲዳማ ቡና ሲሆኑ እንደመጀመርያው ጨዋታ ሁሉ በአንድ ቡድን የበላይነት የተደመደመ ጨዋታ ሆኗል፡፡ የ2005 ቻምፒዮኖቹ መከላከያዎች በቀላሉ 3-0 አሸንፈው ወደ ግማሽ ፍፃሜው አልፈዋል፡፡
የጦሩን የድል ግቦች ምንይሉ ወንድሙ በ12ኛው ፣ ሳሙኤል ታዬ በ44 እንዲሁም ፍሬው ሰለሞን በ86ኛው ደቂቃ ማስቆጠር ችለዋል፡፡
መከላከያዎች ድንቅ እንቅስቃሴ ባሳዩበት ጨዋታ ግብ አስቆጣሪዎቹ ፍሬው ሰለሞን ፣ ምንይሉ ወንድሙ እና ሳሙኤል ታዬ መልካም እንቅስቃሴ ሲያሳዩ ሲዳማ ቡናዎች ተነሳሽነት እና የመጫወት ፍላጎት የጎደለው እቅስቃሴ አድርገዋል፡፡
በግማሽ ፍፃሜው በ2005ቱ ፍፃሜ የተገናኙት መከላከያ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ማክሰኞ ወደ ፍፃሜ ለማለፍ ሲጫወቱ ነገ ደግሞ ወላይታ ድቻ ከ ኤሌክትሪክ ፤ ኢትዮጵያ ቡና ከሀዋሳ ከነማ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ለመግባት ይፋለማሉ፡፡