​የብሔራዊ ቡድናችን ሰሞነኛ ጉዳዮች

በ2018 በኬንያ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የቻን ውድድር ለማለፍ የመጨረሻ የማጣርያ ጨዋታውን ከሱዳን ጋር የሚያደርገው የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን ከውስብስብ ችግሮቹ ጋር በመሆን በአዳማ ከተማ ዝግጅቱን ባልተረጋጋ ሁኔታ ማድረጉን ቀጥሏል፡፡

ከሱዳን ጋር ከነሐሴ 5-7 ባሉት ቀናት የመጀመርያ ጨዋታውን በሀዋሳ ኢንተርናሽናል ስታድየም የሚያደርገው የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን ከሐሙስ ጀምሮ አስቀድሞ ከጅቡቲ ጋር የተጠቀመባቸው 18 ተጨዋቾችን ጨምሮ ለቅዱስ ጊዮርጊሶቹ አስቻለው ታመነ ፣ በኃይሉ አሰፋ ፣ ምንተስኖት አዳነ እና ሳላዲን በርጌቾ  ጥሪ ቢያደረጉም ብሔራዊ ቡድኑ በተሟላ ሁኔታ እየተዘጋጀ እንዳልሆነ ለመመልከት ችለናል ።

አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የተመረጡት ተጨዋቾችን ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር እንዲቀላቀሉ ጥሪ ቢያደርጉም የብሔራዊ ቡድኑ የቡድን መሪ የሆኑት አቶ አበበ ገላጋይ ቀድመው ከጅቡቲ ጋር የነበሩት 18 ተጨዋቾች ብቻ በቂ በመሆናቸው ለሌላ ተጨዋች ጥሪ ማድረግ አያስፈልግም በማለት ትዕዛዝ እንደሰጡ ተነግሯል፡፡ በዚህ ውሳኔ ቅር የተሰኙት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለም በእዚህና በሌሎች ተያያዥነት ባላቸው ችግሮች እንዲሁም ” በስራዬ ጣልቃ እየተገባ የስራ ነፃነት አጥቻለው” በሚል ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር እስከ መስከረም ወር ድረስ ብቻ ቆይተው ከብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝነታቸው ራሳቸውን እንደሚያገሉ መልቀቂያ ማስገባታቸውን ለማወቅ ችለናል።

ብሔራዊ ቡድኑ ከኤሪያ ጋር በገባው ውል መሰረት የቀረበለት ከበዝግጅት ወቅት የሚጠቀሙባቸው አልባሳት ደረጃውን ያልጠበቀ ነው በሚል አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በራሳቸው ወጪ መግዛታቸውም ታውቋል፡፡

አሰልጣኙ መልቀቂያ ለማስገባት ያበቃቸውን ምክንያት እና አሉ በተባሉ ችግሮች ዙርያ አስተያየታቸውን ለመቀበል ሶከር ኢትዮጵያ ዛሬ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም ብትገኝም አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ አስተያየት ለመስጠት ፍቃደኛ አለመሆናቸውን ገልፀዋል።  ያም ሆኖ ከአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ሁኔታ መረዳት የሚቻለው በስራቸው ደስተኛ እንዳልሆኑና ምናልባትም የተለየ ነገር ካልተፈጠረ በቀር ባስገቡት የመልቀቂያ ደብዳቤ አቋሟቸው የሚፀኑ ይመስላል ።

በተፈጠረው ችግር ዙርያ የኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ጁነይዲ ባሻ አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን ችግሩ እንዳለ አምነው በፍጥነት ለተፈጠረው ችግር መፍትሔ ለመስጠት እየሞከሩ እንደሆነ ተናግረዋል። የክልል ሻምፒዮና መክፈቻ ላይ ለመገኘት ወልድያ የነበሩት አቶ ጁነይዲ ከወልድያ እንደተመለሱ ነገ ወደ አዳማ ከተማ በማቅናት ከአሰልጣኞቹ እና ከተጨዋቾቹ ጋር በመነጋገር የቡድኑን መንፈስ ለመጠበቅ ፣ ለማነቃቃት እና አሉ የተባሉ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እንደሚያደርጉ አሰልጣኝ አሸናፊ ወጪ ካወጡም ወጪው በፌዴሬሽኑ እንደሚወራረድ ለሶከር ኢትዮዽያ ተናግረዋል።

ለብሔራዊ ቡድኑ የተሰጠው ግምት እና ትኩረት አናሳ እንደሆነ ብሔራዊ ቡድኑ በሚያደርገው ዝግጅት ላይ መታዘብ ችለናል። ስለሆነም ብሔራዊ ቡድኑ የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ነገር ሁሉ ሊያደርጉለት ይገባል መልክታችን ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *