​የክልል ክለቦች ሻምፒዮና 3ኛ ቀን ውሎ

በኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና 3ኛ ቀን መርሀ ግብር 6 ጨዋታዎች ሲካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች በዝናብ ምክንያት ወደ ነገ ዞረዋል፡፡

ምድብ 1

ዛሬ በወልዲያ መምህራን ኮሌጅ ሊካሄዱ የነበሩ ጨዋታዎች በጣለው ዝናው ምክንያት ሜዳው ለማጫወት ብቁ ባለመሆኑ ወደ ነገ ንጋት 12:30 ተሸጋግረዋል፡፡ በዚህም መሰረት ኢተያ ከተማ ከ ያሶ ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ መልካቆሌ ላይ ሲደረግ የጁ ፍሬ ወልዲያ ከ ሽረ እንዳስላሴ ቢ የሚያደርጉት ጨዋታ በመሐመድ ሁሴን አላሙዲ ስታድየም የሚደረግ ይሆናል፡፡

ምድብ 2

የዚል ምድብ ሁለት ጨዋታዎች በመሐመድ ሁሴን አላሙዲ ስታድየም ሲደረጉ ድሬዳዋ ኮተን እና መርካቶ አካባቢ ተጋጣሚዎቻቸውን በተመሳሳይ 1-0 ውጤት አሸንፈዋል፡፡

08:00 በተደረገው የመተከል ፖሊስ እና የመርካቶ አካባቢ ጨዋታ ጥሩ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት መርካቶዎች በ22 ደቂቃ ይልቃል እጅጉ ከግብ ጠባቂ የተመለሰውን ኳስ ተጠቅሞ ባስቆጠረው ግብ መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ተጭነው የተጫወቱት መርካቶዎች ያገኟቸውን አጋጣሚዎች ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል፡፡ በአንጻሱ መተከል ፖሊስ አምበሉ አብዱሰላም አሚር ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ያገኘውን አጋጣሚ አለመጠቀም ዋጋ አስከፍሏቸዋል።

ቀጥሎ በተካሄደ ጨዋታ ቡሬ ከ ድሬዳዋ ኮተን ተመጣጣኝ የጨዋታ እንቅስቃሴ እና የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት ተስተውሏል፡፡ ድሬዳዋ ኮተን የጨዋታው ብቸኛ የማሸነፍያ ግብ በ17ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ዘሪሁን የአጨራረስ ብቃቱን ተጠቅሞ ማስቆጠር ችሏል።

በ26 ደቂቃ በቡሬው ተጫዋች የሺዋስ ዘውዱ ላይ በተሰራው ጥፋት ሁለቱ ቡድኖች ወደ ግጭት ያመሩ ሲሆን ጨዋታው ለ7 ደቂቃ ያህል ተቋርጧል፡፡ ከቡሬ ዘሪሁን ወልዴ እንዲሁም ተጠባባቂ ወንበር ላይ የነበረው ዮናስ ወርቄ ከሜዳ እንዲወጡ ሲደረግ ከድሬዳዋ ኮተን ያዕቆብ መስፍን በቀይ ካርድ ተወግዷል። በ68ኛው ደቂቃ ላይም በቡሬ ተጫዋች ላይ በተሰራ ጥፋት እንደመጀመሪያው አጋማሽ ባይከርም ግርግር ተነስቶ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ መጎሻሸሞች እና ኃይል የቀላቀለበት እንቅስቃሴ የቀጠለ ሲሆን ከጨዋታው ፍፃሜ ቡኋላ የቡሬ ተጫዋቾች እና የአሰልጣኝ ቡድኑ ከዳኞች ጋር እሰጣ ገባ ውስጥ ገብተው በፀጥታ ኃይሎች ከሜዳ ሊወጡ ችለዋል። ከቡሬ በተጨማሪ ለድሬዳዋ ኮተን ድጋፍ ሲሰጡ የነበሩ ደጋፊዎችም በተመሳሳይ ከፖሊስ ጋር ግብግብ ሲፈጥሩ ተስተውሏል።

ምድብ 4

የምድብ ጨዋታዎች ዛሬ በመልካ ቆሌ ሜዳ የተጀመሩ ሲሆን የቤኒሻንጉሉ ንስር የድሬዳዋው ዋልያን 2-0 በማሸነፍ ምድቡን በድል ጀምሯል፡፡ ቀጥሎ በተደረገው ጨዋታ ደግሞ ሰንዳፋ በኬ ከ አረካ ከተማ 1-1 ጨዋታቸውን ፈጽመዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *