የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና 7ኛ ቀን ውሎ  

የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና በወልዲያ አስተናጋጅነት መካሄድ ከጀመረ አንድ ሳምንት አስቆጥሯል፡፡ በቅዳሜ የ7ኛ ቀን ጨዋታዎችም ወደ 2ኛ ዙር ያለፉ ተጨማሪ ክለቦች ተለይተዋል፡፡

ምድብ 5
በዚህ ምድብ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች መርሳ ከተማን ተከትሎ ወደ ተከታዩ ዙር የሚያልፈውን ቡድን ለይቷል፡፡ መልካ ቆሌ ላይ ሻሾጎ ከተማን የገጠመው ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ 2-0 በማሸነፍ ምድቡን በሁለተኝነት አጠናቆ ወደ 2ኛ ዙር ተቀላቅሏል፡፡

በተመሳሳይ ሰአት መሐመድ ሁሴን አል–አሙዲ ስቴድየም አስቀድሞ ከምድቡ ማለፉን ያረጋገጠው መርሳ ከተማ አላማጣ ከተማን 4-1 በመርታት በ100% ድል ምድቡን አጠናቋል፡፡ በ6ኛው ደቂቃ አዲሴ በላይ ከመሀል የተሻገረውን ኳስ የአላማጣ ግብ ጠባቂ ስህተት ታክሎበት በማስቆጠር መርሳን ቀዳሚ ሲያደርግ በ17ኛው የአላማጣው ግብ ጠባቂ ክንዴ ሽመልስ ከግብ ክልል ውጪ ኳስ በጅ በመንካቱ በቀይ ከሜዳ ወቷል።

በተደጋጋሚ ከመሀል በሚሾልኩ ሰንጣቂ ኳሶች የአላማጣ የተከላካይ ክፍልን ሲረብሹ የነበሩት መርሳዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ከመሀል ያለፈውን ኳስ በ25 ደቂቃ ኪዳኔ ደፋሩ አስቆጥሮ መርሳ 2-0 እንዲመራ አስችሎታል። በ28ኛው የአላማጣው ግብ ጠባቂ የሰራውን የቦታ አያያዝ ስህተት በመጠቀም ከሳጥን ውጭ መሬት ለመሬት አክርሮ በመምታት ኪዳኔ ደፋሩ የመርሳን መሪነት ወደ 3-0 ከፍ አድርጓል።

ከእረፍት መልስ ጫናቸውን ያጠናከሩት መርሳዎች ከእረፍት በተመለሱ በ1 ደቂቃ ውስጥ በሙባረክ ሀሰን ግብ መሪነታቸውን ወደ 4 ከፍ አድርገዋል።
መርሳ ከተማዎች በዚህ የጨዋታ ክፍለ ጊዜም የጨዋታ የበላይነታቸውን ማስቀጠል ቢችሉም ተጨማሪ ግብ ማከል አልቻሉም።

አላማጣዎች ከመጀመሪያ አጋማሽ መጠነኛ የጨዋታ መነቃቃት ቢያሳዩም በ51 ደቂቃ በክንፈ ኪሮስ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ልዩነታቸውን ማጥበብ በዘለለ መፍጠር አልቻሉም።ጨዋታው በመርሳ የበላይነት እና አሸናፊነትም ተጠናቋል።

ምድብ 6
05:00 ላይ የተደረጉት የዚህ ምድብ ጨዋታዎች ሁለቱንም የምድቡ ሀላፊ ቡድኖች ለይቷል፡፡ መልካ ቆሌ ላይ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ሐረር ፖሊስን 4-0 በማሸነፍ ምድቡን በቀዳሚነት ማጠናቀቁን ሲያረጋግጥ መሐመድ አል-አሙዲ ስታድየም ላይ ገንደውሀ ከተማ በኦሮሚያ ፖሊስ 1-0 ቢሸነፍም በ4 ነጥቦች 2ኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ ወደ 2ኛ ዙር ማለፍ ችሏል፡፡

ምድብ 7
08:00 ላይ በተደረጉት ጨዋታዎች ጉለሌ ክፍለ ከተማ ገንፈል ውቅሮን 1-0 በማሸነፍ በቀዳሚነት ምድቡን ሲያጠናቅቅ ተሸናፊው ገንፈል ውቅሮ ተከትሎ ወደ ሩብ ፍፃሜው አልፏል፡፡ መልካ ቆሌ ላይ ካማሺ ቀበሌ 07 ድሬዳዋን 2-1 ማሸነፍ ቢችልም ተያይዘው ከምድቡ ተሰናብተዋል፡፡

ምድብ 8

የዚህ ምድብ ጨዋታዎች 10፡00 ላይ ሲካሄዱ መሐመድ አል-አሙዲ ላይ ቀበሌ 06ን የገጠመው ሺንሺቾ ከተማ 3-0 በማሸነፍ ምድቡን በበላይነት አጠናቋል፡፡ መልካ ቆሌ ላይ ደግሞ ጫንጮ ከተማ ከአቃቂ ማዞርያ ያለግብ አቻ ተለያይቶ በ2ኝነት ሁለተኛውን ዙር ተቀላቅሏል፡፡