ዩራጓይ 2018፡ የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የማጣሪያ ተጋጣሚዎቹን አውቋል

ካፍ ሰኞ የደቡብ አሜሪካዋ ሃገር ዩራጓይ በ2018 ለምታስተናግደው የፊፋ የአለም ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ዋንጫ ለማለፍ የሚደረጉ የአፍሪካ ዞን የማጣሪያ ጨዋታ ድልድሎችን ይፋ አድርጓል፡፡ በቅድመ ማጣሪያ ዙር የተመደበችው ኢትዮጵያ ውድድሯን አዲስ አበባ ላይ ጎረቤቷ ኬንያን በመግጠም እንደምትጀምር የወጣው መርሃ ግብር ያሳያል፡፡ የሁለቱ ሃገራት አሸናፊም በመጀመሪያው ዙር ማጣሪያ ናይጄሪያን የሚገጥም ይሆናል፡፡

በ2016 ዮርዳኖስ ላስተናገደችው የአለም የሴቶች ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ማጣሪያ ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በካሜሮን በመለያ ምት ተሸንፎ ከውድድር መሰናቱ ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያ በተመሳሳይ ፈረንሳይ ለምታስተናግደው የአለም ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ዋንጫ ለማለፍ ከኬንያ ጋር በመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ እንደምትጋጠም ይታወቃል፡፡

በማጣሪያው ላይ የሚሳተፉ ሃገራት ውስን ሲሆኑ 17 የአፍሪካ ሃገራት ብቻ በማጣሪያው ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ 10 ሃገራት በቅድመ ማጣሪያ ሲሳተፉ 7 ሃገራት ደግሞ በቀጥታ ወደ አንደኛው ዙር አልፈዋል፡፡ ሊቢያ፣ ጅቡቲ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሴራሊዮን፣ ጋምቢያ፣ ዛምቢያ፣ ቦትስዋና፣ ማሊ እና አልጄሪያ በቅድመ ማጣሪያ ዙር ውድድራቸውን ሲጀምሩ ናይጄሪያ፣ ቱኒዚያ፣ ጋና፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሞሮኮ፣ ኤኳቶሪያል ጊኒ እና ካሜሮን የማጣሪያ ውድድራቸውን በአንደኛው ዙር የሚጀምሩ ይሆናል፡፡

የቅድመ ማጣሪያ ዙር ጨዋታዎች
(የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች ከጥቅምት 3-5/2010 ባሉት ቀናት፤ የመልስ ጨዋታዎች ከጥቅምት 17-19/2010 ባሉት ቀናት)
ሊቢያ ከ ጅቡቲ
ሴራሊዮን ከ ጋምቢያ
ዛምቢያ ከ ቦትስዋና
ኢትዮጵያ ከ ኬንያ
ማሊ ከ አልጄሪያ

የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች
(የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች ከህዳር 22-24/2010 ባሉት ቀናት፤ የመልስ ጨዋታዎች ከታህሳስ 6-8/2010 ባሉት ቀናት)

1 የሊቢያ እና ጅቡቲ አሸናፊ ከ ቱኒዚያ
2 የሴራሊዮን እና ጋምቢያ አሸናፊ ከ ጋና
3 የዛምቢያ እና ቦትስዋና አሸናፊ ከ ደቡብ አፍሪካ
4 ሞሮኮ ከ ኤኳቶሪያል ጊኒ
5 የኢትዮጵያ እና ኬንያ አሸናፊ ከ ናይጄሪያ
6 የማሊ እና አልጄሪያ አሸናፊ ከ ካሜሮን

የሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች
(የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች ከጥር 25-27/2010 ባሉት ቀናት፤ የመልስ ጨዋታዎች ከየካቲት 9-11/2010 ባሉት ቀናት)
የጨዋታ 1 አሸናፊ ከ ጨዋታ 2 አሸናፊ
የጨዋታ 3 አሸናፊ ከ ጨዋታ 4 አሸናፊ
የጨዋታ 5 አሸናፊ ከ ጨዋታ 6 አሸናፊ

 

ፎቶ – በ2016 ማጣርያ የተሳተፈው ከ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *