ቻን 2018፡ የኢትዮጵያ ተጋጣሚ ሱዳን በአቋም መለኪያ ጨዋታ ተሸንፋለች  

ኬንያ ለምታሰተናግደው ለአፍሪካ ሃገራት ቻምፒዮና (ቻን) ለማለፍ ከሚደረጉት ጨዋታዎች በፊት አንዳንድ ሃገራት የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን እያደረጉ ይገኛል፡፡ ሉሳካ ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከዛምቢያ ጋር ያለግብ አቻ የተለያየ ሲሆን የእሁድ ተጋጣሚው ሱዳን ኪጋሊ ላይ በሩዋንዳ 2-1 ተሸንፏል፡፡

ኪጋሊ በሚገኘው ናያሚራምቦ ስታዲየም የተደረገው ጨዋታ ሃገራቱ ከፊታቸው ላለባቸው ወሳኝ የማጣሪያ ጨዋታ እንዲረዳቸው ተጠቅመውበታል፡፡ የጨዋታው መጀመሪያ ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው የተጫወቱት አማቩቢዎቹ በሶስተኛው ደቂቃ የኤኤስ ኪጋሊው አጥቂ ንሹቲ ሳቪዮ ግብ ቀዳሚ መሆን ሲችሉ ከ15 ደቂቃዎች በኃላ ግን ሱዳን ጨዋታውን ተቆጣጥር ታይቷል፡፡ የሱዳን ብልጫ በ25ኛው ደቂቃ ፍሬ አፍርቶ ነፃ የነበረው ሰይፈዲን ማኪ በግንባር ገጭቶ ባስቆጠረው ግብ ሃገሩን አቻ አድርጓል፡፡ በግቧ የተነቃቁት እንግዶቹ በተደጋጋሚ ወደ ሩዋንዳ የግብ ክልል ከመድረሳቸው ባለፈ በማኪ እና አቡዱልራህማን ማዝ አማካኝነት ለግብነት የቀረቡ ሙከራዎችን አድርገዋል፡፡

 

በሁለተኛው 45 ባለሜዳዎቹ የተወሰደባቸውን ብልጫ ማስመለስ የቻሉ ሲሆን አጥቂው በርናቤ ሙቡምቢ ያመከናቸው እድሎች ሩዋንዳን እስከ75ኛው ደቂቃ ግብ እንዳታስቆጥር አግዷታል፡፡ በኤኤስ ኪጋሊ የሳቪዮ አጣማሪ የሆነው ሙቡምቢ በ75ኛው ደቂቃ ከቢዚማና የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ሩዋንዳን ለድል አብቅቷል፡፡

ሱዳን በመጪው እሁድ ኢትዮጵያን ሀዋሳ ላይ ስትገጥም ሩዋንዳ ወደ ካምፓላ ቅዳሜ ከዩጋንዳ ጋር ትጫወታለች፡፡

ፎቶ – The New Times Rwanda

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *