በክልል ክለቦች ሻምፒዮና ወደ ግማሽ ፍፃሜ ያለፉት ክለቦች ታውቀዋል

የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና በወልዲያ መደረጉን ቀጥሎ ወደ አንደኛ ሊግ ማደጋቸውን ያረጋገጡ 8 ክለቦች ባደረጓቸው የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ወደ ግማሽ ፍጻሜ ያለፉ ክለቦች ታውቀዋል፡፡

ረፋድ 3:00 ላይ በተካሄደው የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ እና ሺንሺቾ ከተማ ጨዋታ አቃቂ 1-0 በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ተሸጋግሯል፡፡ ቀጥሎ በተደረገው ጨዋታም ሌላው የአዲስ አበባ ክለብ ጉለሌ ክፍለከተማ ከ መርሳ ከተማ ጋር በመደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ 2-2 አቻ ተለያይተው በመለያ ምቶች ጉለሌ 4-2 በማሸነፍ ሁለተኛው የግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚ ሆኗል፡፡

በከሰአት መርሃ ግብር በተደረገው የድሬዳዋ ኮተን እና ሰንዳፋ በኬ ጨዋታ ሰንዳፋ 2-1 አሸንፏል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ የሰንዳፋ በኬ ማራኪ የጨዋታ እንቅስቃሴ እና የግብ ሙከራ የበላይነት ቢስተዋልበትም ያገኟቸውን የግብ እድሎች ወደ ግብ መቀየር ሳይችሉ ቀርተዋል። በዚህም ያለምንም ግብ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የተስተዋለ ሲሆን በ65ኛው ደቂቃ ሰንዳፋዎች በማራኪ ቅብብል ይዘው የገቡትን ኳስ ፋሲል ደስታ በጥሩ ሁኔታ አስቆጥሮ ሰንዳፋ መሪ አድርጓል። በ69ኛው ደቂቃ አሰልጣኛቸው ከዳኛ ጋር በፈጠረው አለመግባባት ከሜዳ እንዲወጣ የተደረገባቸው ኮተኖች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ተጭነው በመጫወት በ75ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ዘሪሁን አስቆጥሮ ወደ ጨዋታው ተመልሰዋል፡፡
በጥሩ የመሸናነፍ ስሜት በቀጠለው ጨዋታ በ89ኛው ደቂቃ ሰንዳፋዎች ያገኙት የማእዘን ምት ተሻምቶ ግብ ጠባቂው ሲመልሰው ባቅራቢያው የነበረው ዮሀንስ ጌታቸው አስቆጥሮ ሰንዳፋ 2-1 እንዲያሸንፍ ረድቶታል፡፡ በ90ኛው ደቂቃ በተጫዋቾች መካከል በተፈጠረ ግጭት ከድሬዳዋ ኮተን አብዱ አህመድ እንዲሁም ከሰንዳፋ በኬ ደረጄ አበራ በቀይ ከሜዳ ተወግደዋል።
የእለቱ የመጨረሻ መርሀግብር ወልድያ የጁ ፍሬን ከናኖ ሆርቡ ያገናኘ ሲሆን ናኖ ሁርቡ 2-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡ በመጀመርያው አጋማሽ ሁለቱም ወደ ግብ በተደጋጋሚ ቢደርሱም ግብ ሳይስተናገድ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ በ52ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት ተሻምቶ ሲመለስ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ይዘውት የመጡትን ኳስ ምንተስኖት አብሹ አስቆጥሮ ናኖ ሁሩቡን መሪ አድርጓል። ወልድያዎች ከግቧ መቆጠር በኋላ ብልጫ ተጭነው ቢጫወቱም በ67ኛው ደቂቃ ኤርሚያስ ጥበበ በጭንቅላት ገጭቶ ባስቆጠረው ጎል የናኖ ሁርቡን መሪነት አስተማማኝ አድርጎታል፡፡ የጁ ፍሬዎች ቀሪዎቹን ደቂቃዎች ብልጫ ወስደው ተጭነው መጫወት ቢችሉም ጠንካራ የነበረው የናኖ ተከላካይ አልፎ ግብ ለማስቆጠር ተቸግረዋል።ጨዋታውም በናኖ ሁሩቡ 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *