ጅማ ከተማ የዘጠኝ ተጫዋቾችን ውል ሲያድስ ሶስት ተጨማሪ ተጫዋቾች አስፈርሟል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግን በድል አጠናቆ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያደገው ጅማ ከተማ አዲስ አሰልጣኝ ከመቅጠር ጀምሮ በርካታ ተጫዋቾችን በማስፈረም ላይ ይገኛል፡፡ እስካሁንም የዘጠኝ ተጫዋቾቹን ውል ሲያድስ 11 አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ ቀላቅሏል፡፡

በተጠናቀቀው የውድድር አመት በከፍተኛ ሊጉ ክለብ ሽረ እንዳስላሴ መልካም ጊዜ በማሳለፍ አጋማሽ ላይ ወደ ጅማ አባ ቡና አምርቶ ጥሩ አቋሙን ያሳየው ኄኖክ ኢሳይያስ ወደ ጎረቤት ክለቡ ጅማ ከተማ ማምራቱ ተረጋግጧል፡፡ በቀጣዩ የውድድር አመትም ከገብረመድህን ኃይሌ ጋር በድጋሚ የሚገናኝ ይሆናል፡፡

ሀምበሪቾ የአንደኛ ሊጉን አሸንፎ ወደ ከፍተኛ ሊግ እንዲያልፍ ትልቅ አስተዋጽኦ ካበረከቱት ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ያሬድ አማረ ሌላው ክለቡን የተቀላቀለ ተጫዋች ነው፡፡ ያሬድ በአዲሱ ክለቡ በርካታ ልምድ ያላቸው አዳዲስ አማካዮችን በማስፈረሙ የተሰላፊነት አድል ለማግኘት ከፍተኛ ፉክክር ይጠብቀዋል፡፡

ግብ ጠባቂው ዳዊት አሰፋ የውድድር ዘመኑን በሙሉ በተጠባባቂነት ካሳለፈበት ወልድያ በመልቀቅ አዲሱን የፕሪምየር ሊግ ክለብ ተቀላቅሏል፡፡ የቀድሞው የሐረር ቢራ ፣ መከላከያ እና ንግድ ባንክ ግብ ጠባቂ ለተሰላፊነት በክለቡ ውሉን ካራዘመውና ጥሩ የውድድር ዘመን ካሳለፈው ቢንያም ታከለ ጋር ይፎካከራል፡፡

ጅማ ከተማ ከላይ የተጠቀሱት ሶስት ተጫዋቾችን ጨምሮ ያስፈረማቸው ተጫዋቾች ቁጥር 11 የደረሱ ሲሆን ከዚህ ቀደም ቢንያም ሲራጅ፣ አሸናፊ ሽብሩ ፣ ዮናስ ገረመው ፣ ኄኖክ አዱኛ ፣ ይሁን እንዳሻው ፣ እንዳለ ደባልቄ ፣ ሳምሶን ቆልቻ እና አሚኑ ነስሩን ማስፈረሙ ይታወሳል፡፡


ክለቡ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሲያልፍ ወሳኝ ሚና የተጫወቱ 9 ተጫዋቸች ውላቸውን ያደሱ ሲሆን ግብ ጠባቂው ቢንያም ታከለ ፣ ተከላከዮቹ ኤልያስ አታሮ እና ንጋቱ ገብረስላሴ እንዲሁም አጥቂው ተመስገን ገብረኪዳን ውላቸውን ካደሱት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *