የኢቢሲ ስፖርት ሽልማት በመስከረም ወር መጀመርያ ይካሄዳል

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (EBC) የአመቱ ምርጥ ስፖርተኛ ሽልማት ለመጀመሪያ ጊዜ በሁለት የስፖርት አይነቶች እና በአራት ዋና ዋና ዘርፎች እንደሚሰጥ በይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡

ዝግጅቱን አስመልክቶ ተቋሙ በዛሬው እለት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጠ ሲሆን ምርጥ ወንድ የእግር ኳስ ተጫዋች ፣ በምርጥ ሴት የእግር ኳስ ተጨዋች ፣ ምርጥ ወንድ አትሌት እና ምርጥ ሴት አትሌት ምርጫው የሚካሄድባቸው ዘርፎች መሆኑን አስታውቋል።

አቶ አቤል አዳሙ ፣ ጋዜጠኛ ንዋይ ይመር ፣ አቶ ደመረ አሰፋ እንዲሁም አቶ ጌታሁን ዲማ በኢቢሲ በኩል ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡ ሲሆን አሸናፊው በህዝብ የኤስኤምኤስ መልዕክት ፣ ከጋዜጠኞች ማህበር ከተላኩ ሁለት ጋዜጠኞች እንዲሁም ከፌደሬሽኑ በተመረጡ ግለሰቦች እንደሚሆንና ውጤቱ 70% የሚሆነው ከባለሙያዎች ከሚወሰድ ድምጽ እንዲሁም ቀሪ 30% የሚሆነው ከህዝብ የሚወሰድ ድምጽ መሆኑን አስታውቀዋል።

የእግር ኳስ ተጨዋቾችን በተመለከተ ለእጩነት የተመረጡት ተጨዋቾች በውድድር ዘመኑ በሀገር ውስጥ ሊግ ማለትም በኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ በከፍተኛ ሊግ ወይንም በአንደኛ ሊግ እና በሌሎች ሀገሮች ሊግ የሚጫወቱ ተጨዋቾችን ጨምሮ በብሄራዊ ቡድን ባሳዩት ብቃት እንደተመረጡ ሲገለጽ በስፖርታዊ ጨዋነትም አርአያ የሆኑ ተጨዋቾችን ለማካተት ጥረት እንደተደረገ ተነግሯል።

በጋዜጣዊ መግለጫው በተለይ ኮርፖሬሽኑ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ጋር በተፈጠረው ውዝግብ ዙርያ ከጋዜጠኞች ጥያቄ ቀርቦላቸው ነገሮችን በመነጋገር ለመፍታት እየሞከሩ እንደሆነ እና በፌደሬሽኑ በኩል የተነሳው ጥያቄንም አግባብነት የሌለው መሆኑን ገልፀው በእቅድ ደረጃ ቀደም ብሎ ታስቦበት እየተሰራ ያለ ጉዳይ በመሆኑ እንደማይቀበሉትና እንደ ማንኛውም ተቋም እግርኳሱን ለማሳደግ አስበው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ተናግረዋል።

የሽልማቱ አሸናፊ በመስከረም ወር መጀመሪያ በአይነቱ ልዩ የሆነ ዝግጅት በማዘጋጀት በአራቱም ዘርፎች የዋንጫ ፣ የገንዘብ እና የሰርተፊኬት ሽልማት ለማበርከት እንደታሰበ ሲገለፅ ዝግጅቱም በቀጥታ ስርጭት ለህዝብ እንደሚደርስ ተገልጿል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *