የሴቶች እና ከ17 አመት በታች የጥሎ ማለፍ ውድድሮች ፍፃሜያቸውን አግኝተዋል

 

ደደቢት – የሴቶች ጥሎ ማለፍ አሸናፊ

የኢትዮጵያ ሴቶች ጥሎ ማለፍ ውድድር ዛሬ ፍፃሜውን ሲያገኝ ደደቢት አርባምንጭ ከነማን በቀላሉ 7-0 በማሸነፍ የዋንጫ ባለቤት ሆኗል፡፡

የ2007 የሊጉ ኮከብ ግብ አግቢ ሎዛ አበራ 3 ግቦች አስቆጥራ ሐት-ትሪክ ስትሰራ ሰናይት ባሩዳ (2) ፣ ትእግስት እና ትበይን ቀሪዎቹን ግቦች ከመረብ አሳርፈዋል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ – ከ17 አመት በታች ጥሎ ማለፍ አሸናፊ

ዛሬ በተካሄደው ከ17 አመት በታች ጥሎ ማለፍ ውድድር የፍፃሜ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ባላንጣው ኢትዮጵያ ቡናን 2-0 አሸንፎ የዋንጫ ባለቤት ሆኗል፡፡

ከፍተኛ ውጥረት በነበረበት ጨዋታ ሁለቱም ግቦች የተቆጠሩት ከእረፍት በፊት ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋች ከዳኛ ጋር በፈጠረው ውዝግብ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል፡፡ ተጫዋቹ ዳኛውን ሲማታና ከሜዳ ለመልቀቅ ሲያንገራግር ታይቷል፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊሱ አዲስ አሰልጣኝ ማርቲን ኩፕማን እና ኢትዮጵያ ቡና አዲስ የቀጠራቸው አሰልጣኝ ድራጎን ፖፓዲች በጨዋታው ተገኝተው ታዳጊዎቻቸውን ተመልክተዋል፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስ ከ17 አመት በታች ቡድን በዚሁ የእድሜ እርከን በሚደረገው የሊግ ውድድር በአዳማ ከነማ ተሸንፎ ዋንጫ ማጣቱ የሚታወስ ነው፡፡

 

የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድሮች በቀጣይ ሳምንት ይካሄዳሉ

የኢትዮጵያ ሴቶች አሸናፊዎች አሸናፊ ጨዋታ በቀጣዩ ሳምንት ሀሙስ 10፡00 ላይ ይካሄዳል፡፡ ወንጂ ላይ በተደረገው ውድድር ዳሽንን አሸንፈው የፕሪሚየር ሊጉ የዋንጫ ባለቤት የሆኑት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ዛሬ አርባምንጭ ከነማን አሸንፈው የጥሎ ማለፉን ዋንጫ ያነሱት ደደቢት ለ2007 የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ይፋለማሉ፡፡

ከ17 አመት በታች የአሸናፊዎች አሸናፊ ጨዋታም በተመሳሳይ በቀጣይ ሳምንት ሀሙስ ይካሄዳል፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ ቡናን አሸንፎ ጥሎ ማለፍ ዋጫን ያነሳው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሊጉ አሸናፊ አዳማ ከነማ ጋር 8፡00 ላይ ይጫወታሉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *