ናይጄሪያ እና ሞሮኮ በሰፊ ግብ ልዩነት ሲያሸንፉ ጋና ነጥብ ጥላለች

የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታች አርብም ቀጥለው ሲደረጉ ናይጄሪያ፣ ኬፕ ቨርድ፣ ሞሮኮ እና ቱኒዚያ ድል ሲቀናቸው ጋና በኮንጎ ብራዛቪል በሜዳዋ ነጥብ ጥላለች፡፡

በምድብ አንድ አናት ላይ በተገኙት የቱኒዚያ እና ዲ.ሪ. ኮንጎ ጨዋታ ቱኒዚያ 2-1 አሸንፋለች፡፡ የምድቡንም መሪነት የካርቴጅ ንስሮቹ ከኮንጎ ተቀብለዋል፡፡ ያሲን ሜራህ በፍፁም ቅጣት ምት ቱኒዚያን ቀዳሚ ቢያደርግም እንግዶቹ በቱኒዚያው ግብ ጠባቂ አይመን ማትሉቲ እና የተከላካዮች አለመናበብን ስህተትን ተጠቅመው ወደ እረፍት ከማምራታቸው አስቀድሞ በሴድሪክ ባካምቦ አማካኝነት የአቻነት ግብ አግኝተዋል፡፡ ከእረፍት መልስ ተመጣጣኝ በነበረው ጨዋታ በ48ኛው ደቂቃ የኤስፔራንሱ ኮከብ ጋሂልነ ቻላሊ በፍፁም ቅጣት ምት ውስጥ ያገኘውን እድል በአግባቡ ተጠቅሞ ባስቆጠራት ግብ ቱኒዚያ ዳግም መሪነቱን ጨብጣለች፡፡ በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት ጨዋታው በቱኒዚያ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ምድቡን ቱኒዚያ በ9 ነጥብ ስትመራ፣ ኮንጎ በ6 እንዲሁም ጊኒ በ3 ይከተላሉ፡፡

በምድብ ሁለት ናይጄሪያ የወቅቱን የአፍሪካ ቻምፒዮኗን እና ጎረቤቷን ካሜሮንን 4-0 ረምርማለች፡፡ በጨዋታው መልካም አጀማመር ያደረገቱ የማይበገሩት አንበሶቹ በአጀማመራቸው ሳይፀኑ አራት ግብን አስተናግደው ወደ አለም ዋንጫ ለማለፍ ያላቸውን ተስፋ እየጨለመ መጥቷል፡፡ ጆን ኦቦ ሚካኤል ጥሩ በተንቀሳቀሰበት ጨዋታ ናይጄሪ በኦዲን ኢጋልሆ፣ ኦቢ ሚካኤል፣ ቪክቶር ሞሰስ እና ኬሌቺ ኢያናቾ ግቦች የምድብ መሪነታቸውን አጠናቀዋል፡፡ ናይጄሪያ በተለይ ከ20 ደቂቃ በኃላ ተጋጣሚዋ ካሜሮን ላይ ፍፁም የሆነ ብልጫን መውሰዷ ሶስት ነጥብ እንድታሳካ አስችሏታል፡፡ የካሜሮኑ ግብ ጠባቂ ፋብሪስ ኦንዳ ስራ በዝቶበት ሲያመሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አጥቂው ኤሪክ ማክሲም ቹፖ ሞቲንግ በጉዳት ከሜዳ ወጥቷል፡፡ ናይጄሪያ ምድቡን በ9 ነጥብ ስትመራ ካሜሮን በ2፣ ዛሬ የሚጫወቱት ዛምቢያ እና አልጄሪያ 1 ነጥብን ይዘው ይከተላሉ፡፡

በምድብ ሶስት ሞሮኮ ማሊ ላይ ባልተጠበቀ መልኩ የግብ ናዳን አውርዳ 6-0 ማሸነፍ ችሏለች፡፡ ማሊ በአፍሪካ እግርኳስ ጠንካራ ብሄራዊ ቡድን ካላቸው ሃገራት ተርታ የምትመደብ መሆኗ ሽንፈቱን አስራሚ ያደርገዋል፡፡ ራባት ላይ በተደረገው ጨዋታ የአያክስ አምስተርዳሙ ሃኪም ዘይች ኮከብ ሆኖ አምሽቷል፡፡ በሄርቬ ሬናርድ ለሚሰለጥቱት ሞሮኮ የድል ግቦቹን ሃኪም ዘይች (2)፣ ካሊድ ቢታይብ፣ አሽራፍ ሃኪሚ፣ ፋይሰል ፋጅር እና ሚሞን ማሂ ከመረብ አገናኝተዋል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ በ57ኛው እና 67ኛው ደቂቃ ባካዬ ዲያባሴ እና መሃመድ ኦማር ኮናቴ ከማሊ በሁለት ቢጫ ከሜዳ ተሰናብተዋል፡፡ የዘይች አንድ ግብ የተገኘው በፍፁም ቅጣት ምት ነው፡፡ ከወራት በፊት የማሊ ብሄራዊ ቡድንን ለመልቀቅ ጥያቄ አቅርበው ውድቅ የተደረገባቸው ፈረንሳዊው አሰልጣኝ አለን ጅሬስ በጫና ላይ ይገኛሉ፡፡ ሞሮኮ በ5 ነጥብ ምድቡን ስትመራ ዛሬ ከጋቦን ጋር የምትጫወተው ኮትዲቯር በ4 እንዲሁም ጋቦን በ2 ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡ ማሊ በአንድ ነጥብ የምድቡ ግርጌ ላይ ትገኛለች፡፡

በምድብ አራት ኬፕ ቨርድ ከኋላ ተነስታ አከታትላ ባስቆጠረቻቸው ግቦች ደቡብ አፍሪካን 2-1 አሸንፋለች፡፡ መልካም አጀማመርን ያደረጉት ባፋና ባፋናዎች ቶኬሎ ራንቴ የ14 ደቂቃ ግብ መሪ መሆን ቢችሉም የኑኖ ሮቻ ሁለት ግቦች ፕራያ ላይ ኬፕ ቨርድን አሸናፊ አድርጓል፡፡ በሁለተኛው 45 ኤሪክ ማቶሎ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ በመውጣቱ ደቡብ አፍሪካ ወደ ጨዋታው ለመመልስ እንዳትችል አድርጓታል፡፡ ምድቡን ዛሬ ከሴኔጋል ጋር የምትጫወተው ቡርኪና ፋሶ በ4 ነጥብ ስትመራ ደቡብ አፍሪካ በተመሳሳይ ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጣ ትከተላለች፡፡ ሴኔጋል እና ኬፕ ቨርድ በሶስት ነጥብ ሶስተኛ እና አራተኛ ናቸው፡፡

በምድብ አምስት ጋና ለአራተኛ ተከታታይ ግዜ የአለም ዋንጫ ታሳታፊ የመሆን እድሏ በእጅጉ ተመናምኗል፡፡ ወደ ኩማሲ ያቀናችው ኮንጎ ብራዛቪል ከጋና ጋር 1 አቻ ተለያይታለች፡፡ ቲቪ ቢፎማ ኮንጎን ብራዛቪልን በ17ኛው ደቂቃ ቀዳሚ ሲያደርግ የወረደ እንቅስቃሴን ያሳዩት ጥቋቁር ከዋክብቶቹ ቴዬ ማርቴ የ80 ደቂቃ ግብ አቻ ለመለያየት ተገደዋል፡፡ የጋናው አሰልጣኛ ጄምስ ክዌሲ አፒያ በነሃሴ ወር ከቻን የጋናን ሁለተኛ ቡድንን ይዘው በቡርኪና ፋሶ በሜዳቸው ተሸንፈው ሲወድቁ በአለም ዋንጫ ማጣሪያ ማሳካት የነበረባቸው ነጥብ ሳያሳኩ የጋና የማለፍ ተስፋ በእጅጉ ተመናምኗል፡፡ ምድቡን ዩጋንዳ በ7 ነጥብ
ስትመራ ግብፅ በ6 ነጥብ ትከተላለች፡፡ ጋና እና ኮንጎ በ2 እና 1 ነጥብ ሶስተኛ እና አራተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡

ውጤቶች
ዩጋንዳ 1-0 ግብፅ
ጊኒ 3-2 ሊቢያ
ጋና 1-1 ኮንጎ ሪፐብሊክ
ናይጄሪያ 4-0 ካሜሮን
ኬፕ ቨርድ 2-1 ደቡብ አፍሪካ
ቱኒዚያ 2-1 ዲ.ሪ. ኮንጎ
ሞሮኮ 6-0 ማሊ

ቅዳሜ ነሃሴ 27
15፡00 – ዛምቢያ ከ አልጄሪያ (ሂሮስ ናሽናል ስታዲየም)
17፡00 – ጋቦን ከ ኮትዲቯር (ስታደ ፍራንስቪል)
20፡00 – ሴኔጋል ከ ቡርኪና ፋሶ (ስታደ ሊዮፖልድ ሴዳር ሰንጋሆር)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *