ኮፓ ኮካ ኮላ ዛሬ ሲጠናቀቅ ኢትዮ ሶማሌ እና ደቡብ የዋንጫ ባለቤት ሆነዋል

ከነሀሴ 20 ቀን 2009 ጀምሮ በኢትዮ ሶማሌ ክልላዊ መንግስት መቀመጫ ጅግጅጋ ሲካሄድ የቆየው 3ኛው የኮፓ ኮካ ኮላ ከ15 አመት በታች ሀገር አቀፍ ውድድር በዛሬው እለት በጅግጅጋ ስታድየም ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡ በወንዶች ኢትዮ-ሶማሌ ፣ በሴቶች ደቡብ የዋንጫ ባለቤት ሆነዋል፡፡

ጠዋት 2:00 ላይ በቅድሚያ በደቡብ እና አማራ ክልል መካከል የተደረገው የሴቶቹ የፍጻሜ ውድድር ነበር፡፡ ሁለቱ ቡድኖች በምድብ ጨዋታ 3-3 አቻ መለያየታቸውና በጨዋታው ሶስት ግቦች ለየቡድኖቻቸው ያስቆጠሩት የደቡቧ አምሳል ፍስሀ እና የአማራዋ ትዕግስት ወርቄ መካከል የሚደረገው ፉክክር በጨዋታው ከሚጠበቁ ክስተቶች መካከል ነበር፡፡

ጨዋታው ከተገመተው በተለየ በደቡብ ሙሉ የበላይነት 5-1 በሆነ ሰፊ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ አምሳል ፍስሀም አራት ጎሎችን አስቆጥራ ለደቡብ አሸናፊነት ወሳኙን ሚና ተጫውታለች፡፡ በጨዋታው ድንቅ የነበረችው እየሩሳሌም ሳሙኤል ደግሞ አንዷን ጎል አክላለች፡፡

በመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ በተካሄደ የደረጃ ጨዋታ ኦሮሚያ ከ ድሬዳዋ መደበኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ያለግብ አቻ ተለያይተው ኦሮሚያ በመለያ ምቶች በማሸነፍ በሶስተኛ ደረጃነት ውድድሩን አጠናቋል፡፡

04:00 ላይ የተጀመረው የኢትዮ ሶማሌ እና አማራ ጨዋታ እንደ ሴቶቹ ሁሉ የአንድ ቡድን የበላይነት ታይቶበት በኢትዮ ሶማሌ 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ማሀድ ሀሰን ፣ አብዱላሂ አሚን ፣ ጉሌድ ኢብራሂም እና መሀመድ ሀሰን የኢትዮ ሶማሌ የድል ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል፡፡

የመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ ላይ ለደረጃ በተደረገ ጨዋታ አፋር ከ ድሬዳዋ መደበኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ያለጎል አቻ ተለያይተው በመለያ ምቶች አፋር አሸንፎ የሶስተኛ ደረጃን አግኝቷል፡፡

ከጨዋታዎቹ ፍጻሜ በኋላ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የሽልማት እና የዋንጫ ስነስርአት ተደርጓል፡፡

ወንዶች
ቻምፒዮን – ኢትዮ ሶማሌ (ዋንጫ ፣ የወርቅ ሜዳልያ እና 50,000)
2ኛ ደረጃ – አማራ (የብር ሜዳልያ እና 30,000)
3ኛ ደረጃ – አፋር (የነሀስ ሜዳልያ እና 20,000)
የስፖርታዊ ጨዋነት ዋንጫ (እድሜ) – ሐረር
የስፖርታዊ ጨዋነት ዋንጫ (የጸባይ) – ጋምቤላ
ኮከብ ተጫዋች – አብዱላሂ አሚን (ኢትዮ ሶማሌ – ዋንጫ እና 5,000)
ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ – አብዱላሂ አሚን (ኢትዮ ሶማሌ – ዋንጫ እና 5,000)
ኮከብ ግብ ጠባቂ – ኤልያስ ሙክታር (ኢትዮ ሶማሌ – ዋንጫ እና 5,000)

ሴቶች
ቻምፒዮን – ደቡብ (ዋንጫ ፣ የወርቅ ሜዳልያ እና 50,000)
2ኛ ደረጃ – አማራ (የብር ሜዳልያ እና 30,000)
3ኛ ደረጃ – ኦሮሚያ (የነሀስ ሜዳልያ እና 20,000)
የስፖርታዊ ጨዋነት ዋንጫ (እድሜ) – ድሬዳዋ
የስፖርታዊ ጨዋነት ዋንጫ (የጸባይ) – አዲስ አበባ
ኮከብ ተጫዋች – እየሩሳሌም ሳሙኤል (ደቡብ – ዋንጫ እና 5,000)
ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ – አምሳል ፍስሀ (ደቡብ – ዋንጫ እና 5,000)
ኮከብ ግብ ጠባቂ – ደንቡሽ አባ ( ደቡብ – ዋንጫ እና 5,000)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *